ቀጥታ፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የሚያስችል አውድ የሚፈጥር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የታለመውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የሚያስችል ምቹ መደላደል እንደሚፈጥር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብሔራዊ የዲጂታል ትራስፎርሜሽን ምክር ቤት ሊቀ መንበር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። 

ለስትራቴጂው ውጤታማነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አስገንዝበዋል። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ2030 ስትራቴጂን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።  

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብሔራዊ የዲጂታል ትራስፎርሜሽን ምክር ቤት ሊቀ መንበር ተመስገን ጥሩነህ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠናቀቂያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ይፋዊ ማስጀመሪያ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል። 


 

በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ የማደግ ፍላጎት እና የማደግ አቅም ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

እንደ ሀገር የሚያስፈልገን የማደግ ፍላጎታችንና የማደግ አቅማችንን የሚያገናኝ ስልት ነው ያሉ ሲሆን ይህን የማስተሳሰር አቅም ደግሞ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

መንግስት የዲጂታል ኢትዮጵያ መርሃ ግብርን የዘረጋው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች፣ ከ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ እና ከአፍሪካ አህጉራዊ የትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂዎች መሆኑን አንስተዋል።

በዚሁ መሰረት የተቀረጸው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ወደ ሌላ ምዕራፍ ማሸጋገሩን ገልጸዋል። 

ስትራቴጂው በሀገር ደረጃ የፋይናንስ አሰራርን፣ የአገልግሎት አሰጣጥን፣ የህዝብ ትስስርን፣ የንግድ ስርዓትን፣ የመንግስት ተደራሽነትን፣ የፀጥታ እና ደህንነት አጠባበቅን እንዲሁም የሚዲያ አውድን ጨምሮ የተለያዩ አሰራሮችን መቀየሩን ነው ያመለከቱት። 

የወጣቶች አስተሳሰብ፣ ስነ ልቦና እና አሰራር ተቀይሯል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጠረው አውድ የዲጂታል ዘርፉ እንዲያድግ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።


 

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የተሸጋገረችበት መሆኑን ገልጸው ስትራቴጂው በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን አስታውሰዋል።

አዲሱ ስትራቴጂ በጋራ ጥረት፣ ትጋት እና ትብብር የተጀመሩ የዲጂታል ውጥኖች በፍጥነት የሚስፋፉበት፣ ተናባቢ የዲጂታል ስነ-ምህዳር የሚገነባበት፣ ዘላቂ የዲጂታል እምርታ የሚመጣበትና ሀገራዊ ትራንስፎርሜሽን የሚረጋገጥበት ማዕቀፍ ነው ብለዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዜጎችን ማዕከል ያደረገ መንግስታዊ ስርዓት የበለጠ የሚሰፋበት፣ ሁሉን አቀፍ አካታች የዲጂታል አገልግሎቶች የሚቀርቡበት፣ ሉዓላዊ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ የዲጂታል ስርዓቶች የሚበራከቱበት እንዲሁም የውስጥ ፈጠራ የሚበረታታበት አንደሆነም አስገንዝበዋል። 

ይህም አጠቃላይ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገትና ትራንስፎርሜሽን በማረጋገጥ ወደ ምንመኘው ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚፋጠንበት አውድ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል። 

መንግስት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እንዲተገበር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ እና ሁሉም ባለድርሻ አካል ለስኬታማነቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም