የሚሰጠንን ሀገራዊ ተልዕኮና ግዳጆች በጀግንነት ለመፈጸም ዝግጁ ነን - ተመራቂ ልዩ የኮማንዶ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የሚሰጠንን ሀገራዊ ተልዕኮና ግዳጆች በጀግንነት ለመፈጸም ዝግጁ ነን - ተመራቂ ልዩ የኮማንዶ አባላት
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ የሀገር ሰላምና የሕዝብ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በጀግንነትና በሰብዓዊነት ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን ተመራቂ ልዩ የኮማንዶ አባላት ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊስ አካዳሚው አቅም ያሰለጠናቸውን ልዩ የኮማንዶ ኃይል አባላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በትናንትናው ዕለት በአዋሽ የስልጠና ማዕከል አስመርቋል።
ልዩ የኮማንዶ ኃይሉ ልዩ እና አስቸጋሪ ኦፕሬሽኖችን በእውቀትና በጀግንነት የሚፈጽም መሆኑም በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
ተመራቂ የኮማንዶ አባላቱ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በጀግንነትና በሰብዓዊነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮንስታብል ሚኪያስ ገበያው በሰጠው አስተያየት የወሰዱት ስልጠና የአካል ብቃት ብቻ ሳይሆን የአእምሮ ጽናትና ልዩ የኦፕሬሽን ጥበቦችን ያስጨበጣቸው መሆኑን ገልጿል።
በዚህም የሚሰጠውን ማንኛውንም ሀገራዊ ተልዕኮ በጀግንነት ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሀገርና ህዝብን ከማንኛውም የጥፋት ኃይል የመጠበቅና የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ እስከ መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ሌላኛዋ ተመራቂ ኮንስታብል ምርትነሽ ተካ በሰጠችው አስተያየት የስልጠናው ሂደት ገንቢ፣ አስተማሪና ለቀጣይ ተልዕኮ እንዲዘጋጁ የሚያደርግ መሆኑን ተናግራለች፡፡
ባገኘችው ስልጠና የሚሰጣትን ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመፈጸም ዝግጁ መሆኗንም ገልጻለች፡፡
ኮንስታብል አብዲ ተረፈ በበኩሉ ኢትዮጵያን ከውጪ ባዳ እና ከውስጥ ባንዳ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር የፈጸሙትን ገድል በጀግንነት ለመድገም መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡
ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም የእነሱን ፈለግ በመከተል ሀገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀት እንደሚገባቸው ተመራቂዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ተመራቂዎቹ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተውጣጥተው በጋራ ያሳለፉት የስልጠና ጊዜ የኢትዮጵያን አንድነት በተግባር ያዩበት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡