የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ወጣቱ በአካባቢው ያለውን እምቅ አቅም እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ወጣቱ በአካባቢው ያለውን እምቅ አቅም እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው
ጎንደር፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ወጣቱ በአካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ አልምቶ እንዲጠቀም አዲስ አስተሳሰብና እይታን የፈጠረ ነው ሲሉ በጎንደር ከተማ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ እንዲሁም ገበያን በማረጋጋት ረገድ ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡
በከተማው የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ የሆነው ወጣት አያልነህ ማሩ ለኢዜአ እንደተናገረው፤ ዘርፉ አዋጭና በአጭር ጊዜ ስኬታማ የሚያደርግ ነው፡፡
ቀደም ሲል ሦስት የወተት ላሞችን በመያዝ ወደ ስራ የገባ ቢሆንም ባደረገው ብርቱ ጥረት አሁን ላይ 50 የወተት ላሞችና 35 ጥጆች እንዳሉት ተናግሯል።
በዚህም በቀን 450 ሊትር ወተት ለከተማው በሽያጭ እያቀረበ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ መሆን እንደቻለ ገልጿል።
አሁንም ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግና ለማዘመን የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ወይዘሮ ጽላተ ማርያም ተመስገን በበኩላቸው፤ የሌማት ትሩፋት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በከተማው በዶሮ አርባታ፣ በንብ ማነብና በኩሬ ዓሣ እርባታ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ችለዋል።
በ50 ሺህ ብር ካፒታል የጀመሩት የዶሮ እርባታ ስራ አሁን ላይ ካፒታላቸውን ወደ ሚሊዮኖች ማድረሳቸውን ጠቁመው፤ ከአካባቢ ገበያ ባለፈ ለጎረቤት ሀገር ሱዳን የእንቁላል ምርት እየላኩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በሁለት የንብ ቀፎዎች የጀመረው የንብ ማነብ ስራ አሁን ላይ ወደ 40 የንብ ቀፎዎች ማሳደግ መቻሉን የገለፀው ደግሞ በኢንሼቲቩ በንብ ማነብ ስራ ላይ የተሰማራው ወጣት አበራ ንጉሴ ነው፡፡
በንብ ማነብ ስራውም እስከ 250 ኪሎ ግራም ማር አምርቶ ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለ ጠቁሞ ዘርፉ አዋጭና ያልተነካ የተፈጥሮ ጸጋ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ መላኩ ደምሌ በበኩላቸው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ የአካባቢን ፀጋ መሰረት ያደረጉ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት በ66 ሚሊዮን ብር ወጪ የዶሮ እርባታ ሼዶችን በመገንባት በማህበር ለተደራጁ ዶሮ አርቢ ወጣቶች እንዲተላለፉ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
በከተማው በገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን የተቋቋመው ዘመናዊ የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከወተት አምራቾች በቀን እስከ 10 ሺህ ሊትር ወተት በመረከብ የገበያ እድሎችን መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በከተማው በእንስሳት ማድለብ፣ በወተት ላሞችና በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩ ማህበራት ያጋጠማቸውን የእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በሰዓት 30 ኩንታል መኖ የሚያቀናብር ፋብሪካ ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡