ኢንስቲትዩቱ የግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማሳለጥ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ የግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማሳለጥ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የግንባታ ኢንዱስትሪውን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ለማሳለጥ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የግንባታ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዶ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ የግንባታ ዘርፉን ፕሮጀክት የመፈጸም አቅም ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ ነው።
የግንባታ ፕሮጀክቶች ቀደም ሲል ያጋጥማቸው የነበረውን የጥራት ጉድለት፣ የጊዜ መራዘምና የተጋነነ ወጪ ለመቀነስ ጥናትን መሠረት አድርጎ እየሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል አንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት የበለጠ ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባም አንስተዋል።
ከዚህ አኳያ ኢንስቲትዩቱ የግንባታ ኢንዱስትሪውን በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ለማሳለጥ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ አንዲቀጥል አሳስበዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪውን በሰለጠነ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ለማዘመን እንዲሁም ቀልጣፋ አሰራር ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም።
ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጥራት፣ ጊዜ እና ወጪ ማጠናቀቅ የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ወቅታዊ የግንባታ ዕውቀት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን በማንሳት።