ቀጥታ፡

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ተቋማት የሰላም አካቶ ትግበራን የዕቅዳቸው አካል ሊያደርጉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ተቋማት የሰላም አካቶ ትግበራን በዕቅዳቸውና በሪፖርታቸው አካትተው ሊተገብሩ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመተባበር የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች በህግ ማውጣት፣ በክትትልና በቁጥጥር ሥራዎቻቸው የሰላም አካቶ ትግበራን እውን ማድረግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።

የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ሰላም በአንድ ተቋም ብቻ የሚመጣ ሳይሆን በሁሉም ግለሰቦች፣ ተቋማትና አደረጃጀቶች ውስጥ ያለ አንኳር ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሰላም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር ባለ መስተጋብር ሁሉ የሚገኝ ውጤት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም፣ ሰላም የሚጀምረው እያንዳንዱ ተቋም ኃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት መሆኑን ገልጸው፤ የዚህ ድምር ውጤት የሀገርን ሰላም እንደሚያረጋግጥ አስረድተዋል።

ከቀበሌ እስከ ፌደራል ያሉ የመንግስት መዋቅሮች አገልግሎት ሲሰጡ የህዝብን ፍላጎትና ተጠቃሚነት መሰረት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው፣ ተቋማቱ ሰላምና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በዕቅዳቸው ማካተት፣ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች ሰላምን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ማድረግ እና አገልግሎት አሰጣጥን ለሰላም ግንባታ በሚያግዝ መልኩ መቅረፅ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋማትን ዕቅድና ክትትል ሲገመግም፣ ስራዎቻቸው ለሀገራዊ ሰላም ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ አንጻር ሊቃኝ እንደሚገባ በመድረኩ የተገለፀ ሲሆን የሰላም የቁጥጥር ስርዓትን ባህል ማድረግም የሰላም አካቶ ትግበራን ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑም ተጠቅሷል።

በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም