ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ሕዝብን አንድ በሚያደርጉ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በውክልና ሥራዎች ሕዝብን አንድ በሚያደርጉ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመተባበር የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች የሕግ ማውጣት፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ሲያከናውኑ የሰላም አካቶ ትግበራን እውን ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሰላም ለሀገር ዕድገት መሠረት መሆኑን አንስተዋል።

ይህም ለአርሶ አደሮች ምርታማነት፣ ለነጋዴው ትርፋማነት፣ ለመንግሥት የልማት ውጤታማነትና ለተመራማሪዎች አዳዲስ የፈጠራ ሐሳብ ለማመንጨት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰላም በሁላችንም እጅ ያለ እንጂ ከየትም የምናመጣው አይደለም ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ የሀገራችንን ሰላም መጠበቅ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰላም ግንባታ የሀገር ግንባታ ሥራ መሆኑን በመግለጽ፤ እየታየ ያለውን ሀገራዊ ሰላም ለማፅናት ሀገራዊ ልማትን ማፋጠን ይገባል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ በውክልና ሥራዎች እና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች ሕዝብን አንድ በሚያደርጉ የሰላም ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ምክር ቤቱ የተቋማትን የሰላም አካቶ ትግበራ መሠረት በማድረግ ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሕጎች ሲቀርቡለት ለሰላም ያላቸውን ሚና ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀታቸውን ይቆጣጠራል ብለዋል።

ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት ለምን ዓላማ አዋሉት የሚለውንም ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም