ቀጥታ፡

በአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

በምድብ አንድ ማሊ ከዛምቢያ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ማሊ በአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ ለ14ኛ ጊዜ ሲሆን ዛምቢያ 19ኛ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።

ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

እ.አ.አ በ1994 በቱኒዚያ በተካሄደው 19ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተገናኝተው ዛምቢያ 4 ለ 0 አሸንፋለች።

ማሊ የአፍሪካ ዋንጫን አሸንፋ አታውቅም። ዛምቢያ አንድ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ሆናለች። 

በዚሁ ምድብ ትናንት በተደረገ ጨዋታ አዘጋጇ ሞሮኮ ኮሞሮስን 2 ለ 0 አሸንፋለች። 

በምድብ ሁለት ደቡብ አፍሪካ ከአንጎላ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በማራካሽ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አምስት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ደቡብ አፍሪካ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

አንጎላ በአህጉራዊው መድረክ ደቡብ አፍሪካን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማሸነፍ ትጫወታለች።

የአንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ደቡብ አፍሪካ 12 ተሳትፎዋን ታደርጋለች።

በአፍሪካ ዋንጫው ለ10ኛ ጊዜ የምትሳተፈው አንጎላ ወደ ጥሎ ማለፍ ከመግባት የዘለለ ታሪክ የላትም።

በምድብ ሁለት ሌላኛው መርሃ ግብር ግብጽ ከዚምባቡዌ ምሽት አምስት ላይ በአጋዲር ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሀገራቱ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት የነበሩትን ሁለት ጨዋታዎች ግብጽ አሸንፋለች። 

ግብጽ የአፍሪካ ዋንጫን ሰባት ጊዜ በማንሳት ስኬታማዋ ሀገር ናት። የዘንድሮውን ጨምሮ በአፍሪካ ዋንጫ ለ27ኛ ጊዜ በመሳተፍ የተሳትፎ ክብረ ወሰን ባለቤት ነው።

ተጋጣሚዋ ዚምባቡዌ ለስድስተኛ ጊዜ ተሳትፎዋን ታደርጋለች። ብሄራዊ ቡድኑ በተሳትፎዎቹ ላይ ከምድቡ አልፎ አያውቅም ።

ጨዋታዎቹ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም