የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትልሞች በሦስት ዋና ጉዳዮች ያተኩራሉ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትልሞች በሦስት ዋና ጉዳዮች ያተኩራሉ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018(ኢዜአ)፡- የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትልሞች በዋናነት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠቃለያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በይፋ የማስመጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ወቅትም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዋና ራዕዩን ሰብሰብ አድርገን ስንገልጸው ሦስት ነገሮችን ለማሟላት ያለመ ነው ብለዋል።
በዚህም መሠረት የመጀመሪያው አቅርቦት(አክሰስ) መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ማለት ሁሉም ዜጎች ካሉበት ሆነው የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ዜጎች እኩል እድል እና እኩል አገልግሎት እንዲያገኙ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የመጀመሪያ ትልሙ አቅርቦት ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ዕድል(ኦፖርቹኒቲ) መሆኑን አመላክተው፤ እኩል እድል ባልሰጠንበት መስክና ሁኔታ እኩል ተጠቃሚ መሆን አይቻልም ነው ያሉት በማብራሪያቸው።
በጾታ፣ በአካል ጉዳት ወይም በርቀት ምክንያት ዜጎች ሊያገኙ የሚገባውን እድል እኩል የሚያመቻች ሥርዓት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው ያስገነዘቡት።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እንዲያሳካ ከሚፈለጉት ጉዳዮች አንዱ ለዜጎች እኩል እድል መስጠት መሆኑንም አመላክተዋል።
ሦስተኛው ዲጂታል ኢትይጵያ 2030 እንዲያሳከው የሚፈለገው ትልም መተማመን(ትረስት) መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በዜጎችና በተቋማት መካከል መተማመን ካልተፈጠረ፤ የገንዘብ ዝውውር፣ መማር ማስተማር፣ ለጤና ዳታ መስጠት፣ ደፍሮ ለሥራ ማመልከት፣ የግል መረጃን በክላውድ ላይ ማስቀመጥ የሚታሰብ አይደለም ሲሉ አብራርተዋል።
ቴክኖሎጂ አሳላጭ መሆን ተስኖት በጥርጣሬ የሚታይና የሚፈራ ብሎም ዜጎች የማያምኑበት ከሆነ የምናስበውን ነገር አያሳካም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በገለጻቸው።
ሦስቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትልሞች አቅርቦት፣ ዕድል እና መተማመን ተደምረው ለዜጎች በርከት ያለ የሥራ ዕድል መፍጠር ብሎም ለሀገር ዕድገት ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል።
ሥራ እና ዕድገት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ሉዓላዊነትንም የሚያረጋግጥ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
ስለዚህ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ከላይ በተገለጹት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የኢትዮጵያን ብልጽግና ከሚያረጋግጡ ዋና ዋና ሴክተሮች(ምሠሦዎች) አንዱ ሆኖ ያገለግላል ተብሎ በመንግሥት መታሰቡን አውስተዋል።
በመሆኑም በትብብር ከሠራን ይህን ራዕይ እንደምናሳካ ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉም ተናግረዋል።
#DigitalEthiopia2030