ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን ለማሳካት የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኮኔክቲቪቲ ተደራሽነት ጉዳዮች ወሳኝ ናቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018 (ኢዜአ)፡- የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን ለመሳካት የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኮኔክቲቪቲ ተደራሽነት መሟላት ሲችሉ ብቻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠቃለያ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ገለጻ አድርገዋል።

በዚሁ ወቅትም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይ(አቅርቦት፣ ዕድል እና መተማመን) ሊሳኩ የሚችሉት ወሳኝ የሆኑት የኤሌክትሪክ ኃይል እና ኮኔክቲቪቲ ተደራሽነት ሲሟሉ ብቻ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ማለት ስልክ፣ መኪና እና ድሮንን ጨምሮ ለተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ምግብ መሆኑን በመገንዘብ በአግባቡ ማቅረብ ይገባል፤ ካልሆነ ግን ቴክኖሎጂው የሚጠበቅበትን አገልግሎት መስጠት አይችልም ብለዋል።

ስለዚህ የቴክኖሎጂዎች ምግብ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የሚዳረስበት መንገድ የግድ ናሽናል ግሪድ መሆን እንደማይጠበቅበት አመላክተዋል።

በዚህም መሠረት አንዳንዱን በሚኒ ግሪድ፣ አንዳንዱን በኦፍ ግሪድ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ ለምሳሌ በተሻገረ ገጠር ሥራችን ላይ በየአርሶ አደሩ ቤት የፀሐይ ኃይል(ሶላር ሲስተም) እንዲስፋፋ እየተሞከረ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የሶላር ሴል ማምረት መጀመሯንና በወር ከ20 እስከ 25 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ለውጪ ገበያ እያቀረበች መሆኗን አመላክተው፤ ይህን ሴል የሚቀረውን ነገር በማሟላት በኢትዮጵያ ገጠር ውስጥ እንዲስፋፋ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

በአጭሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ሳናሟላ የምናረጋግጠው እድገት አይኖርም ነው ያሉት።

የተሟላ እድገት ለማምጣት ኢነርጂ ያስፈልጋል፤ ያ ኢነርጂ ግን በከተሞችና በቅርብ ርቀት የታጠረ ሳይሆን ሁሉም ዜጎች የሚያገኙት መሆን አለበት ብለዋል።

እንዲሁም ኮኔክቲቪቲ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትልሞች መሳካት የጎላ ሚና እንዳለው በመጠቆም፤ በርከት ያሉ ከተሞች 4ጂ እና 5 ጂ ኔትዎርክ መጠቀም መጀመራቸውን አውስተዋል።

ኮኔክት የሚደረግበት መንገድ የ4ጂ እና 5ጂ እንደተጠበቀ ሆኖ በገጠራማው አካባቢዎች በቀላሉ በፋይበር ኦፕቲክስ እንዲሁም አሁን በምንጠቀምባቸው ቴክኖሎጂዎች የማንደርስባቸው ከሆኑ የሳተላይት አማራጮችን የምንጠቀምበትን መንገድ መከተል ያስፈልጋል ብለዋል።

በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ኢትዮጵያን መቶ በመቶ ኮኔክት ማድረግ አለብን፤ ይህ ደግሞ ይቻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደሚቻል አምነን ኮኔክት ማድረግ ካልቻልን በስተቀር ዜጎች እኩል ዕድል ማግኘት አይችሉም ሲሉ ገልጸዋል።

ለሁሉም ዜጎች እኩል እድል እንዲረጋገጥ ደግሞ ኤሌክትሪክ እንደ ምግብ፤ ኮኔክቲቪቲ እንደ ኢኳላይዘር ተወስዶ በትጋት ልንሠራበት የሚገባ ሴክተር ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

ይህን ስናሳካ እና እውቀት ስንጨምርበት ነው ያልነውን ትልም በተሟላ መንገድ ልናረጋግጥ የምንችለው ብለዋል።

#DigitalEthiopia2030

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም