ቀጥታ፡

ከዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማት አንጻር በሦስት ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018(ኢዜአ)፡- ከዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማት (ኢንፍራስትራክቸር) አንጻር በሦስት ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ማጠቃለያ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም፤ የዲጂታል መሠረተ ልማትን በሚመለከት ዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማት(ዲፒአይ) እና ኪ ፐብሊክ ኢንፍራስትራክቸር(ኬፒአይ) በሚል በሁለት ተከፍሎ እንደሚታይ ጠቁመዋል።

አሁን እኛ የምናተኩረው ዲጂታል ፐብሊክ ኢንፍራስትራክቸር (ዲፒአይ) ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ከእነዚህ መካከል ዋና ዋና ተብለው የሚገለጹት ፋይዳ፣ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት እና ዳታ ኤክስቼንጅ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተቋማትና በሌሎችም መካከል መረጃን ማስተሳሰር (ዳታ ኤክስቼንጅን) ካላረጋገጥን የምናስበውን የተሟላ ሥርዓት አንፈጥርም ሲሉ አስገንዝበዋል።

በዚህ አግባብ እያንዳንዱ ተቋም እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማየት ያለበት ሲስተም አለኝ ወይስ የለኝም ሳይሆን ሲስተሜ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተደገፈ ነው ወይ የሚለውን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በኤ አይ ካልተደገፉ የዲጂታል ኢንፍራስትራክቸሮቻችን እያሉ እንደሌሉ ይሆናሉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በገለጻቸው።

ስለሆነም ይህ እንዳይሆን የፋይዳን ጉዳይ አበክረን በመሥራት መቶ በመቶ ማዳረስ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪም የክፍያ ሥርዓቶቻችን የሚናበቡ መሆን አለባቸው፤ በባንኮች መካከል፣ በመንግሥት ተቋማት መካከል፣ በመንግሥትና በግል የተለየ ዳታ ሌየር መካከል የዳታ ኤክስቼንጅ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

እነዚህን ማከናወን ካልተቻለ ግን ዲጂታል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያግዝ መሆን አይችልም፤ ማኑዋል የነበረውን ነገር በኮምፒውተር ማድረግ ብቻም በቂ አይደለም ሲሉ አስገንዝበዋል።

#DigitalEthiopia2030

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም