ቀጥታ፡

በአፍሪካ ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ አዘጋጇ ሞሮኮ ኮሞሮስን አሸነፈች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታ ሞሮኮ ኮሞሮስን 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ማምሻውን በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ብራሂም ዲያዝ በ55ኛው እና አዩብ ኤል ካቢ በ74ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

ተቀይሮ የገባው ኤል ካቢ በመቀስ ምት ግሩም ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ዲያዝ የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጎል ባለቤት ሆኗል።

ሞሮኮ በ11ኛው ደቂቃ ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት ሶፊያን ራህሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የሞሮኮ አምበል ሮማን ሳይስ በ19ኛው ደቂቃ በጉዳት ምክንያት በጃዋድ ኤል ያሚክ ተቀይሮ ወጥቷል። ተጫዋቹ በቁጭት ስሜት ያለቀሰበት መንገድ ትኩረትን ስቧል።

በጨዋታው ላይ ሞሮኮ በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድል በመፍጠር ከፍተኛ ብልጫ ወስዳለች።

በአንጻሩ ኮሞሮስ በጥልቀት በመከላከል እና ኳስ በቀሙበት አጋጣሚ በፈጣን ሽግግር ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ውጤታማ አልሆነም።

በጨዋታው ወቅት የጣለው ዝናብ በቡድኖቹ አጨዋወት ላይ መስተጓጎል ፈጥሯል።

የኮሞሮሱ ተከላካይ ያኒስ ካሪ የውድድሩን የመጀመሪያ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል።

ውጤቱን ተከትሎ አዘጋጇ ሞሮኮ ምድብ አንድን በሶስት ነጥብ ጀምራለች።

በዚሁ ምድብ ማሊ ከዛምቢያ ነገ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከሞሮኮ እና ኮሞሮስ ጨዋታ በፊት ደማቅ እና በቀለም ያሸበረቀ የመክፈቻ ስነ ስርዓት በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ተደርጓል።

35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

24 ሀገራት በስድስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም