ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018(ኢዜአ)፡- ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ የተሳካ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠናቂቀያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በይፋ የማስመጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በገለጻቸውም፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሲነደፍ በዲጂታል ሴክተር ስትራቴጂ አውጥቶ የመተግበር ልምድ ብዙም ስላልነበረን አይሳካም የሚል ፍራቻ እንደነበር አውስተዋል።
ይሁን እንጂ በሚያስደንቅ ሁኔታ ከአምሥት ዋና ዋና ዘርፎች መካከል አንዱ ስትራቴጂ መሆን አለበት ለኢትዮጵያ ብልጽግና አይተኬ ሚና አለው ከሚለው ውሳኔ ጀምሮ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ዲጂታልን ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከቱሪዝም እና ከማዕድን አስተካክሎ የማየት ዕይታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ኋላም ስትራቴጂው ተነድፎ የተተገበረበትን መንገድ ስንመለከት በግብርና፣ በማዕድን ብሎም በኢንዱስትሪው እንደተገኘው ስኬት በዲጂታሉ ዘርፍም ተገኝቷል ብለዋል።
በመሆኑም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ የተሳካ ስትራቴጂ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ይህን ስትራቴጂ በመንግሥት መዋቅር ብቻ ሳይሆን አካዳሚውም እንዲፈትሸው እጋብዛለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።
ስትራቴጂው ምን ነበር ትልሙ(ንድፉ)?፣ ምን ተሳካ?፣ ምን አልተሳካም? የሚለው ሲታይ፤ አንድን ነገር አርቆ ማለም(ማቀድ) ብቻ ሳይሆን የመከወን ብቃት ከዚያ ውስጥ እንዴት ሊወጣ እንደሚችል ያመላከተ አስተማሪ ጉዞ ነበርም ነው ያሉት።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መንደርደሪያ ያደረገውም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን መሆኑን ጨምረው አስታውቀዋል።
#DigitalEthiopia2030