የግሉን ዘርፍ እና ስታርታፕን በማበረታታት የዳታ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የግሉን ዘርፍ እና ስታርታፕን በማበረታታት የዳታ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018(ኢዜአ)፡- የግሉን ዘርፍ በተለይም ስታርታፕን በማበረታታት የዳታ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠቃለያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በይፋ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ገለጻ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ገለጻ፤ ሉዓላዊነት በየዘመኑ ካለ ጉዳይ ጋር እያደገ የሚሄድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዛሬ 100 ዓመታት በፊት ሉዓላዊነት ከድንበር ማስከበር ጋር የተያያዘ ሃሳብ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ በራሳቸው ምግባቸውንና ሃሳባቸውን የማያመርቱ ሀገራት ስለ ሉዓላዊነት ሊያወሩ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
አሁን ባለንበት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘመን ሉዓላዊነት ዳታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዳታን መቆጣጠር እና ከሀገራት ፈቃድና ፍላጎት ውጪ ሌሎች እንዳይጠቀሙበት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አህጉራችን አፍሪካ የሁሉም ቴክኖሎጂ ግብዓቶች መገኛ ብትሆንም ከሌሎች ሀገራት በምታስገባቸው ቺፕስን የመሰሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ምክንያት የዳታ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ አለመቻሏን አንስተዋል፡፡
በአፍሪካ ጥቂት የማይባሉ ሀገራት ሲስተሞቻቸውን ከሌሎች ሀገራት በማምጣት የሚጠቀሙ በመሆኑ ከሀገራት ጋር በሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሲስተም መዘጋት ሲያጋጥምና ይህም የሀገራትን እንቅስቃሴ ሲያግድ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡
ይህንን ለመቅረፍ የአፍሪካን አቅም ለመጠቀም እንቅስቃሴ መጀመሩንና ለዚህም በኢትዮጵያ የተጀመረውን የፋይዳ እና ቴሌብር ቴክኖሎጂ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ገበያ ለማቅረብ ድርድር መጀመሩን ለማሳያነት አንስተዋል፡፡
የዳታ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል የግል ኩባንያዎችና ስታርታፖች በአፍሪካ ገበያ እንዲወዳደሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የዳታ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል የግል ኩባንያዎች እና ስታርታፖች በአፍሪካ ገበያ እንዲወዳደሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዚህም የዳታ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሌላውን የመጠቀም አቅማችን እያደገ ይሄዳል ብለዋል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም ተቋማትና ኃላፊዎች የግሉን ሴክተር በተለይም ስታርታፖችን በቴክኒክ፣ በገንዘብ እና የገበያ እድል በማመቻቸት መደገፍና ወደ ገበያ ገብተው ትርፋማ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
#DigitalEthiopia2030