ቀጥታ፡

ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመታገል ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን እንሰራለን - የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

ሰቆጣ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመታገል ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን እንሰራለን ሲሉ በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በሰቆጣ ከተማ “ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቆማለን” በሚል መሪ ሀሳብ የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በአካባቢው በነበረው የሰላም እጦት ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርገው መቆየታቸውን አንስተዋል።

በጥፋት ተግባር ላይ የተሰማራው ቡድን የአካባቢውን ህብረተሰብ ለጉዳት ዳርጎ መቆየቱን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፣ መንግስት ህግን ለማስከበር ባከናወናቸው ተግባራት ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ደምሴ ገብሬ እና ወይዘሮ ስንዳዩ አስረሱ፣ መንግስት የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሰራ ያለውን ተግባር አድንቀው፣ የሰላምን ጥሪ በመቀበል እየመጡ ያሉ ታጣቂዎችም ከጥፋታቸው በመማር ህዝብን ለመካስ መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

ከክልሉ ፖሊስ በጡረታ የተገለሉት የከተማው ነዋሪ ኮማንደር አዱኛ ወዳጅ በበኩላቸው "የእኔ ብቻ" የሚል አስተሳሰብ ለሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን በመገንዘብ አምርረን በመታገል ማስተካከል የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ሹመት ጥላሁን፣ ለሰላም ግንባታ ከመንግስት ጥረት ባለፈ የህብረተሰቡ እገዛና ትብብር ውጤት አምጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም በጫካ የቀረው ቡድን የመንግስትን የሰላም አማራጭ ተቀብሎ እንዲመጣ የህብረተሰቡ ጥረት መኖር እንዳለበት አንስተው በቀጣይም ለሰላም አጥብቀው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል፣ ጽንፈኛው ቡድን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር አፍራሽ ተልዕኮ አንግቦ እየሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በመሆኑም ይህን የጥፋት ተልዕኮ ህዝቡ ተገንዝቦ ህግ በማስከበር ሂደት ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ይህንንም አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የብሔረሰብ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም