ቀጥታ፡

በከተሞች የሚገኙ ወንዞችን በማልማት ለዕድገት መጠቀም እንደሚቻል ተመክሮ ቀስመናል - የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጉባኤ ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ በከተሞች የሚገኙ ወንዞችን በማልማት ለቱሪዝም መስህብ ማዋል፣ ለገቢ ምንጭነትና ለመዝናኛ አገልግሎት መጠቀም እንዲሚቻል ተመክሮ መቅሰማቸውን የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።

በከተሞች የኮሪደር ልማት ላይ ትኩረት ያደረገው የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጉባኤ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

 

በጉባዔው ላይ የተሳተፉ የተለያዩ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘውን የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡


 

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አንዱአለም ጤናው፤ የኢትዮጵያ ከተሞች የዕድገት ጉዞ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

የትብብር መድረኩ ዓላማ ከተሞች ዕድገትና ልማታቸውን ለማሳለጥ በሚያደርጉት የለውጥ ጉዞ ልምድና ተሞክሯቸውን በመለዋወጥ የተሻለ እመርታ እንዲያሳዩ ማገዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ በማደግ ላይ ያሉ ከተሞች ልምድ የሚቀስሙበትን ምቹ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡


 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ አካባቢ ጠበላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ታረቀኝ ገቸረ(ዶ/ር)፤ በአዲስ አበባ እየተከናወነ ከሚገኘው የወንዝ ዳርቻ ልማት በርካታ ተሞክሮ መቅሰማቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም የተበከሉና የቆሻሻ መጣያ የሆኑ ወንዞችን በማልማት ለቱሪዝም መስህብነት፣ ለገቢ ምንጭነትና ለመዝናኛ አገልግሎት ማዋል እንዲሚቻል ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


 

በኦሮሚያ ክልል የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፍቅሩ ነግሶ፤ የኮሪደር ልማት አካል የሆነው የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት የአይቻልም አስተሳሰብን የሰበረና የተሻለ ስራ መስራት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡


 

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሽቱ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ በተመለከቱት የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት መደነቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም መፍጠርና መፍጠን የሚለውን የመደመር መንግስት አቅጣጫ በተግባር ያሳየና ለሌሎች ከተሞች እድገትና ልማት አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተመለከቱት የልማት ስራ በአካባቢያቸው ባለው ፀጋ በመጠቀም የተሻለ ልማት ማከናወን እንደሚቻል ግንዛቤ የወሰዱበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደር አመራሮች አባላት ያገኙትን ተሞክሮ በአካባቢያቸው ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም