ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን-የንግዱ ማህበረሰብ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን-የንግዱ ማህበረሰብ አባላት
ወልዲያ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የወልዲያ ከተማ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።
በወልዲያ ከተማ "የንግዱ ማህበረሰብ ለዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
በውይይቱ ከተሳተፉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መካከል ሃጅ አህመድ ሃሰን እንደገለጹት፤ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ መወያየት መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
ለንግዱ ማህበረሰብ ትልቁ ትርፉ ዘላቂ ሰላም በመሆኑ ለከተማችንና ለአካባቢያችን ሰላም አጥብቀን እንሰራለን ብለዋል።
መንግስት በአካባቢው ሰላምን ለማጽናት በሚያደርገው ጥረት የንግዱ ማህበረሰብ ድርሻ የጎላ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አጥብቀው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ መንግስት ሠላምን በማጽናት ህዝቡ ሠላማዊ ኑሮውን እንዲመራ የህግ የማስከበር ስራውን ማጠናከሩን ገልጸዋል።
የንግዱ ማህበረሰብም ለሰላም መስፈን የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ንጉሥ ዝናቡ በበኩላቸው ፤ ሰላምን ለማጽናት ሁሉም ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመሆኑም መንግስት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ የንግዱ ማህበረሰብ ድርሻውን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የክልሉና የወልዲያ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።