የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኤሊት ፖሊስ ኃይል መገንባቱ የፀጥታ ሪፎርማችን ትልቅ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኤሊት ፖሊስ ኃይል መገንባቱ የፀጥታ ሪፎርማችን ትልቅ ማሳያ ነው
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በተልዕኮው ልዩና ስትራቴጂያዊ የሆነ ኤሊት ፖሊስ ኃይል መገንባቱ የፀጥታ ሪፎርማችን ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አካዳሚ በራሱ አቅም ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የኮማንዶ ፖሊስ አባላት የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘቴና ይህንን ጀግና የፖሊስ ሠራዊት በመመልከቴ የተሰማኝ ደስታ ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
መንግሥታችን በፀጥታ ዘርፉ ባከናወነው መጠነ-ሰፊ ሪፎርም፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዛሬ ለሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጠንካራ ዘብ፣ በሙያው ብቁና በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በሕዝብ ፍቅርና አመኔታ የተገነባ ፕሮፌሽናል ተቋም ሆኗል ሲሉም ገልጸዋል።
ይህ ኤሊት የፖሊስ ሠራዊት ማንኛውንም ውስብስብና አስቸጋሪ የጸጥታ ስጋቶችን በአጭር ጊዜና በከፍተኛ ብቃት የመቀልበስ ልዩ አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል።
የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም የሚፈታተኑ የሽብርና የከባድ ወንጀል ሙከራዎችን በብቃት የመከላከልና መቆጣጠር ኃላፊነት ተጥሎበታል ሲሉም አስታውቀዋል።
ሀገራችን በሁሉም መስክ ለምታስመዘግበው ድል ዋነኛው መሠረት ሰላምና ፀጥታ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው።
ለዚህ ሰላም ሲሉ ሕይወታቸውን እስከመስጠት የደረሰ መስዋዕትነት ለከፈሉና ሀገርን ለማጽናት በቁርጠኝነት ለቆሙ የፖሊስ አባሎቻችን ትልቅ ክብር እንደሚገባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
የእስካሁኑ ስኬት ይበልጥ ለሥራ የሚያተጋ መሆኑንም አመላክተዋል።
በመጪው ግንቦት የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ ሆኖ እንዲከናወን እንደ COP32 ያሉ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መድረኮች እንዲሁም ደማቅ የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የፌዴራል ፖሊስ ኃይላችን የተጣለበትን ታሪካዊ አደራ በብቃት እንደሚወጣ ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።
የዛሬ ተመራቂ የኤሊት ፖሊስ ሠራዊት አባላት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ምልክት ናችሁ ሲሉም አስረድተዋል።
ሀገርንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከየትኛውም አደጋ የመከላከል ኃላፊነታችሁን በታማኝነት እንድትወጡ አደራ ማለት እፈልጋለሁ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።