ቀጥታ፡

ልዩ የኮማንዶ ኃይላችን ልዩ እና አስቸጋሪ ኦፕሬሽኖችን በእውቀትና በጀግንነት የሚፈጽም ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ ልዩ የኮማንዶ ኃይላችን ልዩ እና አስቸጋሪ ኦፕሬሽኖችን በእውቀትና በጀግንነት የሚፈጽም ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በአካዳሚው ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ልዩ የኮማንዶ አባላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ዛሬ በአዋሽ የማሰልጠኛ ማዕከል አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ተመራቂዎቹ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመለመሉ ሲሆኑ፤ ላለፉት 16 ወራት ልዩ ፖሊሳዊ ስልጠና ወስደዋል።


 

በዚህ ልዩ የኮማንዶ ስልጠና ማናቸውንም ልዩ ኦፕሬሽኖች እና ግዳጆች መወጣት የሚያስችል ጠንካራ አቅም መፍጠራቸውንም ጠቅሰዋል።

ፖሊስ በሕግ፣ በአሠራር፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በውስጥና በውጪ ግንኙነት ስኬታማ ሪፎርም ማካሄዱን አንስተዋል።

በዚህም የሀገር አለኝታ የሆነ፣ ገለልተኛና ሙያዊ ብቃት እና የመፈጸም አቅም ያለው፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የፖሊስ ተቋም መገንባቱን ገልጸዋል።

በተለይም በከፍተኛ ትኩረት ከተሠሩ ተግባራት መካከል የሰው ኃይሉ ወቅቱ የሚፈልገውን የተሟላ ፖሊሳዊ እውቀት፣ ክህሎት እና ስብዕና እንዲላበስ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋማትን ማሳደግ ችለናል ነው ያሉት።


 

የፖሊስ ኃይሉ ባለፉት ጊዜያት በሀገር እና በሕዝቦቿ ላይ በባንዳ እና በባዳ የተቃጡ ሀገር የማፍረስ ሴራዎችን ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ማክሸፉንና ሰላምን ማረጋገጡን ገልጸዋል።

ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሰላምን ለማደናቀፍ የማይተኙ መሆናቸውን አመልክተው፤ ማናቸውንም ሀገራዊ ግዳጆች በብቃት እና በቁርጠኝነት ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን ብለዋል።

ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በስኬት ለማጠናቀቅ የፖሊስ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል።

የልዩ ኮማንዶ ኃይል ተልዕኮ ብርታትን፣ ትዕግስትን፣ የመንፈስ ጽናትን፣ እምነትንና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።

የተልዕኮውን ክብደት በአግባቡ በመገንዘብ በስልጠና ወቅት ባሳዩት ብቃት፣ የአዕምሮ ጽናት፣ እውቀትና ክህሎት ሙያቸውን በብቃትና በቁርጠኝነት በተግባር እንዲወጡም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም