ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለሁሉም ዓይነት ፈተናዎች ሁሌም ዝግጁ የሆነ የፀጥታ ኃይል ገንብታለች 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዓይነት ፈተናዎች ሁሌም ዝግጁ የሆነ የፀጥታ ኃይል መገንባቷን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊስ አካዳሚው አቅም ያሰለጠናቸውን ልዩ የኮማንዶ ኃይል አባላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ዛሬ በአዋሽ የስልጠና ማዕከል አስመርቋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የለውጡ መንግሥት ውጤታማ ከሆነባቸው የሪፎርም ሥራዎች አንዱ በፀጥታ ተቋማት ላይ ተግባራዊ የሆነው ሪፎርም መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሪፎርም የፀጥታ ተቋማት ንቁ፣ ብቁና ቴክኖሎጂ የታጠቁ እንዲሆኑ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በስልጠና እና በአደረጃጀት የተሻለ ሂደት ተጉዘናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዓይነት ፈተናዎች ሁሌም ዝግጁ የሆነ ኃይል እንዲኖራት አድርገናል ብለዋል።

ዛሬ የተመረቁት ልዩ ኮማንዶዎችም የዚህ ውጤት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

በሪፎርሙ መሠረት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጠበቃ የሆነ፣ በሙያው የሚኮራ፣ ሕጎችን በአግባቡ በመተግበር በሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ያለው ጠንካራና በቴክኖሎጂ የተደራጀ ተቋም እየገነባ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የሪፎርም አካል የሆነውን ልዩ የኮማንዶ ፖሊስ ለመጀመሪያ ጊዜ በራስ አቅም አሰልጥኖ በዛሬው ዕለት ማስመረቁም የተቋማዊ አቅሙ ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህ ኃይል የትኛውንም ወንጀል በመከላከልና የሀገርን ብልጽግና የማሳካት ብቃት ያለው ነው ብለዋል።


 

በቀጣይ ከሀገራችን ዕድገት ጋር የተጣጣመ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚመጥን የፖሊስ ተቋም ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የዛሬ ተመራቂ ልዩ የኮማንዶ ፖሊስ አባላት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ማረጋገጫ የሆነውን ሕገ መንግሥት የማክበር እና የማስከበር ከፍተኛ ኃላፊነት አለባችሁ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመደመር የሚመራው ፖሊስ ሕዝብን ያከብራል፣ ያገለግላል፣ ይጠብቃል፣ ለሕዝብም መስዋዕትነት ይከፍላል ብለዋል።

ከነገዋ የበለፀገች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ለመሆን ብልጽግናን የሚያሳልጥ ኃይል ሆኖ መገኘት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ይህም ዛሬ የተመረቁ የፖሊስ አባላት ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

የልዩ ኮማንዶ ፖሊስ ተመራቂዎች የቀሰሙትን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና በተገቢው መንገድ በመጠቀም ሕዝብንና ሀገርን በቅንነት፣ በታማኝነትና በጀግንነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም