በአማራ ክልል ስትራቴጂካዊ ምርቶች የሚያመርቱ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች በስፋት ወደ ሥራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ስትራቴጂካዊ ምርቶች የሚያመርቱ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች በስፋት ወደ ሥራ ገብተዋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ስትራቴጂካዊ ምርቶች የሚያመርቱ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች በስፋት ወደ ሥራ መግባታቸው ተገለጸ።
የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል በደብረ ብርሃን ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን በመጎብኘት ላይ ነው።
በጉብኝቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና ከፍተኛ የመንግስት አመራር አባላት ተገኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ከለውጡ በኋላ በአማራ ክልል ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባት በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ተጨማሪ አዳዲስ ፋብሪካዎችም ሥራ ለመጀመር ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
የነባር ኢንዱስትሪዎችም የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አመልክተው፤ አዲሶቹ ደግሞ ስትራቴጂካዊ ምርቶችን የሚያመርቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ መንግስት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ በአገሪቷ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በደብረ ብርሃንና በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞች በኢንዱስትሪው ዘርፍ እያከናወኑት ያለው ተግባር ውጤታማ መሆኑን መመልከታቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ የአገሪቷን ገቢ በማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለዘርፉ በቂ ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ በከተማው ያለውን ምቹ የኢንዱስትሪ ሁኔታ ተከትሎ በርካታ ፋብሪካዎች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ጥቂት ወራትም 14 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባታቸው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል።
ከንቲባው በከተማው የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሌሎች ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የዛሬው ጉብኝትም የደብረ ብርሃንን የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማነቃቃትና ውጤታማ የማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።