ቀጥታ፡

በፈጠራ ሥራው ለብዙኃን ብርሃን የፈነጠቀው ወጣት 

ብዙዎች ችግርን ሲያማርሩ ጥቂቶች ግን ችግርን ወደ ዕድል ይቀይሩታል።

ወጣት ፌደሳ ሹማ ከእነዚህ ጥቂት ባለ ራዕይ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ በኢትዮጵያ የተሰራ በሚል ስም ድምጽና ጭስ አልባ ዘመናዊ ጄነሬተሮችን የሚያመርተው "ፌዶ ፓወር ሶሉሽን" (Fedo Power Solution) ባለቤት ነው፡፡

የወጣቱ የጥረትና የፈጠራ ውጤት ዘመናዊና ለአካባቢ ተስማሚ ጄኔሬተር ሲሆን፤ ወጣት ፌዴሳ ምርቱን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ሕልም ሰንቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወጣቶች በሰመር ካምፕ የሰሯቸውን የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በተመለከቱበት ወቅት፤ ሀገር የምትሻገረው ከትንሽ ተነስተው ወደ ትልቅ ኩባንያዎች በሚያድጉ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የፈጠራ ስራዎቹ ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት እንደሚጥሉ ጠቅሰው፤ የተመለከቱት ጄኔሬተር አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደረጎ ተጨማሪ ነዳጅ ሳይጠቀም ለበርካታ ሰዎች ብርሃን መስጠት የሚያስችል ድንቅ የፈጠራ ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉ የፈጠራ ስራዎች ኢትዮጵያውያንን ወደ ተሻለ አኗኗር የሚያሸጋግሩ ናቸው ነው ያሉት፡፡


 

የፌዶ ፓወር ሶሉሽን መስራች ወጣት ፌደሳ ሹማ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው፤ የፈጠራ ስራውን የጀመረው በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በስራው ላይ በፈጠረበት ተግዳሮት የተነሳ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ ለስራው ይጠቀምበት የነበረው ጄኔሬተር ነዳጅ የሚጨርስ፣ ድምፁ የሚረብሽና ጭስ የሚያወጣ መሆኑ ለወጣቱ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖበት እንደነበርም ያስታውሳል፡፡

ይህንኑ ችግር ለማቃለል መፍትሄ መፈለግ የጀመረው ወጣት ፌደሳ በ2014 ዓ.ም የራሱን ጄኔሬተር በመሥራት የፈጠራ ሕልሙን ዕውን ማድረጉን ተናግሯል፡፡ 

ወጣቱ በፈጠራ ሥራው ለመጀመሪያ ጊዜ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ውድድር አሸናፊ በመሆን የፈጠራ አቅሙን መረዳት እንደቻለ ያስታውሳል፡፡

ከዛም በዞን፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የተደረጉ የፈጠራ ውድድሮችን በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የ260 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ማግኘቱ ለስራው ማደግ የራሱ ሚና እንደነበረው ጠቅሷል፡፡ 

ይህ ሽልማት ለትልቅ ሕልሙ መነሻ እንደሆነው የሚናገረው ወጣት ፌደሳ፤ መጀመሪያ በ300 ኪሎ ዋት የጀመረው የፈጠራ ሥራ ዛሬ ወደ 600 እና አንድ ነጥብ አምስት ሜጋ ዋት መሸጋገሩንም ተናግሯል፡፡

ፌዶ ፓወር ሶሉሽን የሚያመርታቸው ጄኔሬተሮች ድምፅና ጭስ አልባ መሆናቸው ለአካባቢ ጥበቃና ለጤና ተስማሚ አድርጓቸዋል።

ጄኔሬተሩ በኤሌክትሪክም ሆነ በሶላር(በፀሐይ ኃይል) ቻርጅ መስራት የሚችል ሲሆን፤ ወጪ ቆጣቢና በአንድ ጊዜ ቻርጅ ረጅም ጊዜ የሚያገለግልና ለማንኛውም ተቋም የሚመጥን ነው ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ፌዶ ፓወር ከ60 በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና በቀን የተለያየ አቅም ያላቸውን 100 ጄኔሬተሮች ለማምረት እየሠራ እንደሚገኝም አንስቷል፡፡ 

የሰነቅኩት ሕልም በዚህ አያበቃም የሚለው ወጣቱ "በኢትዮጵያ የተመረተ" የሚል ታሪካዊ አሻራ ያረፈባቸውን ምርቶች ወደ አፍሪካና ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት የመላክ ትልቅ ራዕይ መሰነቁንም ይናገራል፡፡

ወጣት ፌደሳ ሹማ በመንግሥት እየተደረገለት ላለው ድጋፍ አመስግኖ፤ ወጣቶች የጀመሩትን የፈጠራ ሥራ ተስፋ ሳይቆርጡ እንዲገፉበትና ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ እንዲተጉ ጥሪውን አስተላልፏል።

የሀገር ዕድገት የሚረጋገጠው በፈጠራና በዕውቀት ሽግግር ነው የሚለው ወጣቱ፤ የኢኖቬተሮች ሚና ለኢትዮጵያ ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።


 

የፌዶ ፓወር ሶሉሽን ቺፍ ቴክኒሽያን ኦፊሰር ሄኖክ አማኑኤል በበኩሉ፤ ድርጅቱ የሚያመርታቸው ጄኔሬተሮች ዋነኛ የኃይል አማራጭ መሆን መጀመራቸውን ጠቁሟል፡፡

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ጄኔሬተሮች ለሆስፒታሎች፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለመንግስትና ለግል ተቋማት ጥቅም መስጠት እንደሚችል ጠቅሷል፡፡  


 

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስታርታፕና ኢኖቬቲቭ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ ሙሉጌታ ውቤ፤ በኢትዮጵያ የስታርታፕ ስነ-ምህዳሩ በከፍተኛ ሁኔታ መነቃቃት እያሳየ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ስታርታፖችን ለመደገፍ ስታርታፕ ኢትዮጵያ እና ስትራይድ ኢትዮጵያ የተባሉ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት አቅማቸውን እንዲያሳዩና ትስስር እንዲፈጥሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስታርታፖች ወደ ኢንኩቤሽን ማዕከላት ገብተው ስራዎቻቸውን እንዲያበለጽጉና በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠራ ስራዎቻቸውን እንዲያሳዩ  ዕድል መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡

ስታርታፖች የፈጠራ ስራዎቻቸውን አሳድገው ወደ ምርት እንዲገቡ እገዛ እየተደረገ መሆኑን አስታውሰው፤ ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

የስታርታፕ የፈጠራ ውጤቶች የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም