ቀጥታ፡

የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላችንን እንወጣለን- የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች

ጭሮ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ በዞኑ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።

ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች የተወጣጡና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ህዝባዊ የውይይት መድረክ ዛሬ በጭሮ ከተማ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በዞኑ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በመጓተቱ ህብረተሰቡ ከልማቱ እንዳይጠቀም ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የለውጡ መንግስት ይህን ችግር በመፍታት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ ለህዝብ ጥቅም እንዲውሉ ማድረጉን አንስተዋል።

በመድረኩ አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል የሀብሮ ወረዳ ገለምሶ ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ መሀመድ እንዳሉት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የአርብቶ አደሩን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ያደረጉ የውሀ ተቋማት፣ የመንገድና የገበያ ማዕከላት ተገንብተዋል።

የለውጡ መንግስት የአርሶአደሩን ኑሮ የሚቀይሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በማከናወን ለአገልግሎት ማብቃቱን የተናገሩት ደግሞ የቦኬ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አያን ሐሰን ናቸው።


 

ይሁን እንጂ በወረዳቸው ከፍተኛ ሆስፒታል ባለመኖር የህክምና አገልግሎት በቅርበት በተሟላ መልኩ እንዳያገኙ በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

መንግስት የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት መስራቱ በገጠርና በከተሞች የብልፅግና ጉዞን ለማፋጠን እያገዘ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጡሎ ወረዳ ነዋሪ መሐመድ አሚን አብዱላሂ ናቸው።


 

ሀገራዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ለስኬት እንዲበቁ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኢክራም ጠሀ በበኩላቸው፤ በዞኑ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአጭርና በረጀም ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በዞኑ አንጫር ወረዳ የህብረተሰቡን የሆስፒታል ጥያቄ ለመመለስ  በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆስፒታል ለመገንባት የመሬት ርክክብ መደረጉን ተናግረዋል።

የጭሮ  አጠቃላይ ሆስፒታል የአገልግሎት ደረጃን ለማሻሻልም የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ ሥራ መጀመሩንም አስታውሰዋል።


 

በዞኑ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ሶስት ተጨማሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት  መታቀዱንም አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት በበኩላቸው ፤ የህብረተሰቡን ጥያቄ በህዝባዊ ውይይቶች  ለማዳመጥ  መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በመደመር እሳቤ  የተከናወኑ ልማቶች ብልፅግናን ለማረጋገጥ  አቅም መሆናቸውንም አንስተዋል።  

 የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ በተለያየ መንገድ የጀመረውን እገዛም እንዲያጠናክር አቶ ዳንኤል አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም