በትግራይ ክልል ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያደናቅፉ አካላትን ህብረተሰቡ አጥብቆ መታገል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያደናቅፉ አካላትን ህብረተሰቡ አጥብቆ መታገል አለበት
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ሰላም ለመስፈን የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚያደናቅፉ አካላትን ህብረተሰቡ አጥብቆ ሊታገላቸው እንደሚገባ ስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ገለጸ።
የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምክር ቤት እና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አባል ጣዕመ አራዶም ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍንና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዳይተገበር እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላትን የክልሉ ህዝብ በፅናት ሊታገላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስት የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ በትግራይ ክልል ሰላም እንዲሰፍንና ልማት እንዲመጣ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በተለይም ለክልሉ አስፈላጊውን የልማት በጀት መመደቡ፣ የባንክ፣ የጤና እና የማህበራዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀመሩ ማድረጉ፣ የፈረሱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን መልሶ መገንባቱን አውስተው፤ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው በመመለስ ረገድ የፌዴራል መንግስት ላከናወናቸው ተግባራት አድናቆት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ቡድን መንግስት ተፈናቃዮችን ለመመለስና ሰላም ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት እያደናቀፈ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይህ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ እነዚህን እንቅፋቶች በትጋት እንዲታገል ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
ስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በመጪው ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ሙሉ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ጣዕመ፤ የእጩዎች ምልመላና አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ-ምርጫ ሂደቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ምርጫው መካሄዱ የትግራይ ህዝብ በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ተገቢውን ውክልና ማግኘት እንደሚያስችለውም ነው የገለጹት።
የክልሉ ህዝብ እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ሁሉ በዴሞክራሲ፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ የሚሆነው በምርጫ የህዝብ ውክልና ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነም አስታውቀዋል።
የፌዴራል መንግስት በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እስካሁን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።