ቀጥታ፡

የተካሄዱት ሕዝባዊ ውይይቶች የታሰበውን ግብ አሳክተዋል - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018 (ኢዜአ)፡- አራት ዓላማዎችን እንዲያሳኩ የተካሄዱት ሕዝባዊ ውይይቶቹ የታሰበውን ግብ መምታታቸውን የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳን (ዶ/ር) አስታወቁ።

"‎የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ህዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡

የሕዝባዊ ውይይቶቹን አንድምታ አስመልክቶ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ የተካሄደውን ሕዝባዊ ውይይት የመሩት ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ እንደ መደመር መንግሥት አራት ዓላማዎችን ማሳካት አለብን በሚል ወደ ሕዝባዊ ውይይቶቹ ተገብቷል ብለዋል።

በዚህም የመጀመሪያው ዓላማ የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት የሠራቸውን ሥራዎች፣ ያሳካቸውን ዕቅዶችና ያስመዘገባቸውን ድሎች ሕዝቡ ሊገነዘብ በሚችልበት ደረጃ እናቅርብ የሚል መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህን ተከትሎም ሕዝቡ ሀገራዊ አጀንዳዎችንና ትላልቅ ስኬቶችን ተገንዝቦ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት እንዲችል ማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከጉባ ብሥራቶች በፊትም እንደ መንግሥት የተመዘገቡ ስኬቶችን ለሕዝቡ ፊት ለፊት በማቅረብ ማሳወቅም የመጀመሪያው ዓላማ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁለተኛው ዓላማ መንግሥትና ሕዝብን ፊት ለፊት ማገናኘት መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ አግባብ መንግሥት ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን አድማጭም ስለሆነ ሕዝቡን እናዳምጠው የሚል መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት ሕዝቡ ፍልጎቱን፣ መሻቱን፣ ቅሬታውን፣ ጥያቄዎቹንና ወደ ፊት እንዲስተካከሉለት የሚፈልጋቸውን ነገሮች እንዲያቀርብ ዕድል መስጠት ተችሏል ብለዋል።

እንዲሁም ሦስተኛው ዓላማ በቀጣይ ትላልቅ ነገሮች ስላሉ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ፤ ሕዝብም ከፊታችን ላሉ ትላልቅ የጉባ ብሥራቶች፣ ሂደቶች እና ውጤቶች የሚጠበቅበትን ሚና እንዲያበረክት የሚያስችል የጋራ ተልዕኮ መስጠት ነው ብለዋል።

በዚህ አግባብ የጋራ መዳረሻ ላይ ከተስማማን በኋላ መንግሥትም የቤት ሥራውን ወስዶ እንዲሠራ ሕዝብም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት የጋራ ተልዕኮ መስጠት የመድረኩ ሦስተኛ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል።

አራተኛው ዓላማ የተሳሳተ መረጃ የሚሰጡ፣ የሚያደናግሩ የሚዲያ ዘመቻዎች፣ በግራም በቀኝም የተቀናጁ የሕዝብን መረጋጋት ሊነሱ፣ የሕዝብን ግንዛቤ ሊያዛቡ የሚችሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ማስገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል።

ስለዚህ ሕዝቡ ከአፍራሽ መረጃዎችና ዘመቻዎች እራሱን ቆጥቦ ከእውነትና ከእውቀት ጋር እንዲቆም የጋራ አቋም ማስያዝ አራተኛው ዓላማ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በአጠቃላይ በሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች፣ በማኅበራዊ ልማት፣ በከተማ ልማትና በሌሎች የልማት እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች የተሠሩ ሥራዎችን፣ የመጡ ውጤቶችን ሕዝቡ መገንዘቡን በመድረኮቹ ድምጹን ከፍ አድርጎ ተናግሯል ብለዋል።

እንዲሁም በሚቀጥሉት ጊዜያት መንግሥት ያቀደውን የሚሠራ ከሆነ እኛም ዐቅማችን በፈቀደ መጠን ከመንግሥት ጎን እንቆማለን የሚል የጋራ አቋም የተያዘበት መድረክ መሆኑንም አመላክተዋል።

እንደመደመር መንግሥት አራት ዓላማዎችን እንዲያሳኩ የተካሄዱት ሕዝባዊ ውይይቶቹ የታሰበውን ግብ መምታታቸውን ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም