ቀጥታ፡

የሲዳማ ክልል ቡና ላኪ አርሶ አደሮች ከባለ ልዩ ጣዕም ቡና ልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሰሩ ነው

ሐዋሳ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ ከባለ ልዩ ጣዕም ቡና ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ቡናን በጥራት ለመሰብሰብ ትኩረት መስጠታቸውን በሲዳማ ክልል የበንሳ ወረዳ ቡና ላኪ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

የክልሉ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን በበኩሉ በክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ ከሚቀርበው ቡና 20 ከመቶ የሚሆነው ባለልዩ ጣዕም ቡና እንዲሆን ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡ 


 

በሲዳማ ክልል የበንሳ ወረዳ ቡና ላኪ አርሶ አደሮች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ከባለልዩ ጣእም ቡና ልማት  ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ግብዓትና የባለሙያ ድጋፍ በመጠቀም እየሰሩ ነው።

የባለልዩ ጣዕም ቡና ልማትን በጥራት ማከናወናቸው በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድሮች አሸናፊ እንዳደረጋቸውና ምርታቸውንም  በከፍተኛ ዋጋ  በመሸጥ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንደቻሉ ገልጸዋል።፡ 

በበንሳ ወረዳ የቦምቤ ቀበሌ ቡና ላኪ አርሶ አደር በቀለ ቡጡሻ በ15 ሄክታር መሬታቸው ላይ ከልጆቻቸው ጋር በመሆን ቡና  እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 


 

በዚህም ለባለልዩ ጣዕም ቡና ትኩረት በመስጠታቸው  ከሁለት ዓመት በፊት  የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር አሸናፊ በመሆን አንድ ኪሎ ቡና 102 ሺህ ብር ለመሸጥ እንደቻሉ አስታውሰዋል፡፡ 

በዚህም 302 ኪሎ ግራም ቡና ለሽያጭ አቅርበው ከፍተኛ ገቢ ማግኘታቸው ልማቱን ለማስፋፋት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡ 

በዘንድሮ ዓመትም ከ192 ኩንታል በላይ የባለልዩ ጣዕም ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ  የግብዓትና ባለሙያ ድጋፍ በመጠቀም ቡናን በጥራት መሰብሰብ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ሌላኛው ቡና ላኪ አርሶ አደር ንጉሴ ናሬ በበኩላቸው፤ ላለፉት አምስት ዓመታት ቡናቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ 


 

የግብዓትና የባለሙያ ድጋፍ ተጠቅመው በ30 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት የባለልዩ ጣዕም ቡና ያገኙትን ውጤት  ለአካባቢው አርሶ አደሮች በተሞክሮነት በማስፋት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በዘንድሮ ዓመትም ከ384 ኩንታል በላይ ቡና በማቅረብ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ጥራትን መሰረት ያደረገ ምርት እየሰበሰቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

አርሶ አደሩ ከሦስት ዓመት በፊት በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር ካቀረቡት የባለልዩ ጣዕም ቡና ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘታቸውን አስታውሰው ውድድሩ በዘርፉ እያከናወኑ ያሉትን ልማት ለማጠናከር አቅም መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡ 

በየዓመቱ ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡት የባለልዩ ጣዕም ቡና የሚያገኙት ገቢ እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ቡና ላኪ አርሶ አደር በላይነህ ባሪሶ ናቸው፡፡ 


 

ዘንድሮም ከ12 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ካለሙት ቡና ከ130 ኩንታል በላይ ጥራት ያለው ቡና ለማምረት  የባለሙያ ድጋፍ ተግባራዊ ማድረጋቸውን  ተናግረዋል፡፡ 

የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው፤ በክልሉ በዘንድሮው ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ ከሚቀርበው 40 ሺህ ቶን ቡና 20 ከመቶው ባለልዩ ጣዕም ቡና እንዲሆን ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 


 

ለዚህም በክልሉ ባለፈው ዓመት 264 የነበረውን የላኪ አርሶ አደሮች ቁጥር ወደ 759 በማሳደግና ቡና አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ የባለልዩ ጣዕም ቡና ምርትና ጥራትን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ 

ከ2012 እስከ 2016 በተካሄደው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የባለልዩ ጣዕም ቡና ውድድር የክልሉ አርሶ አደሮች ቀዳሚ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ በግብረ ሃይል የታገዘ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በአዘጋጁ አገር በጥራታቸው የላቁ አሸናፊ ቡናዎችን ውድ በሆነ ዋጋ በግልፅ ጨረታ የሚሸጥበት የጥራት ውድድር ነው። 

ውድድሩ እ.አ.አ 1999 በብራዚል እንደተጀመረና ላለፉት ዓመታትም በተለያዩ ቡና አምራች ሃገራት ሲካሄድ መቆየቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም