ቀጥታ፡

የዲጂታል መሰረተ ልማት መስፋፋት የከተሞችን ምጣኔ ሃብታዊ እና ማህበራዊ እድገት እያፋጠነ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የዲጂታል መሰረተ ልማትን በመገንባት እና በማስፋፋት የከተሞችን ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ እድገት እያፋጠነ እንደሚገኝ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ገለፀ።

መንግስት በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማሳካት የሚያስችሉ መሰረታዊ መደላድሎችን ለመፍጠር በርካታ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የከተሞች ሁለንተናዊ እድገት እውን የሚሆነው የአሰራር ስርዓትን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ ሲቻል ነው።

ሚኒስቴሩ የከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

መንግስት የዲጂታል መሰረተ ልማትን በመገንባት እና በማስፋፋት የከተሞችን ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት እያፋጠነ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት።

በዚህም ዜጎች ያለምንም መጉላላት ጉዳያቸውን በቀላሉ ማስፈፀም የሚችሉባቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የማስተዋወቅና የማላመድ ስራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።

ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የሚሰጡትን አገልግሎቶች ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በቅርቡም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሃዋሳና ሌሎች ከተሞች የኦን ላይን አገልግሎት በስፋት መጀመሩን ገልፀው፤ በቀጣይ በተለያዩ ከተሞች አገልግሎቱ ተደራሽ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ዜጎች ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ቦታ የሚያገኙበት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች በሁሉም ክልሎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ማዕከሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በማጣመር በአንድ ጣራ ስር  የሚሰጥበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የሚሰጡ አገልግሎቶች ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው የተናገሩት።

ሚኒስቴሩ በ2018 በጀት ዓመት የከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያቀላጥፍ አዲስ ሶፍትዌር በማበልፀግ በሁሉም ከተሞች ስራ ለማስጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም