ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ልማትና ሰላሟ በዓባይ ወንዝና በቀይ ባሕር ላይ ከሚኖራት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጋር የተቆራኘ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ልማትና ሰላሟ በዓባይ ወንዝና በቀይ ባሕር ላይ ከሚኖራት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ(ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ግርማ ሰይፉ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ዓባይ እንጂ “ናይል” በሚል ስያሜ የሚጠራ ወንዝ እንደሌላትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በመፃረር መቆም ታሪክ ይቅር የማይለው የሀገር ክህደት መሆኑም ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።

አቶ ግርማ ሰይፉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤት ሀገር ናት፤ ሆኖም በአንድ ወቅት በነበሩ የሀገር መሪዎች በህገወጥ መንገድ ከተፈጥሯዊ የባሕር በሯ እንድትገለል ተደርጓል።

በአሁኑ ወቅት የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ አጀንዳ መደረጉ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ የባሕር በር የማስመለስ አጀንዳም የዘመኑ ትውልድ የታሪክ አደራ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በውጭ ሀገሮች ድጋፍ ጭምር በሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ስም የሚደረጉ ጫናዎች የሁለቱ ውሃዎች ፖለቲካ ድምር ውጤት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለተፋሰሱ ከዓባይ ወንዝ 86 ከመቶ በላይ ውሃ እንደምታበረክት የገለጹት አቶ ግርማ፤ ኢትዮጵያ ዓባይ እንጂ “ናይል” በሚል ስያሜ የሚጠራ ወንዝ እንደሌላት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያሏት ዓባይና የዓባይ ገባር ወንዞች እንጂ “ናይል“ አለመሆኑን ጠቁመው፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ለሚፈሱ ወንዞች የሚሰጥ ስያሜም የተሳሳተ ትርክት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የልማትና የሰላም ምንጭ በዓባይ ወንዝና በቀይ ባሕር ላይ ሊኖር ከሚችል ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጋር የሚያያዝ መሆኑንም አብራርተዋል።

ግብጽ ነጣጣይ እና የተቃርኖ አካሄድን የሚከተሉ የኢትዮጵያ ኃይሎችን በመደገፍ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ተጠቃሚ እንዳትሆን የያዘችው አቋም የዓባይን ውሃ በብቸኝነት የመቆጣጠር ፍላጎት መሆኑን አንስተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት በትልቅ ሀገራዊ አጀንዳነት የተወሰደና የትውልድ ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ለሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት መከበር በሁሉም መስክ መስራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

በርካታ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ለሀገራቸው ጥቅምና ፍላጎት መከበር የሚሰሩ መኖራቸውን አመልክተው፤ ከዚህ በተቃራኒ የሚቆሙ ጥቂቶች ከታሪክ ተወቃሽነት እራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም