ከሕዝባዊ ውይይቶቹ በቂ ሐሳብ ሸምተናል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ከሕዝባዊ ውይይቶቹ በቂ ሐሳብ ሸምተናል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018(ኢዜአ)፡- መንግሥት በየአካባቢዎቹ እያከናወነ ስላለው ልማት ብሎም ማኅበረሰቡ ቢስተካከሉ ስላላቸው ጉዳዮች በሕዝባዊ ውይይቶቹ በቂ ሐሳብ ሸምተናል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።
"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ህዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡
የውይይት መድረኮቹን አንድምታ አስመልክቶ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰውን(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል።
በሎጊያ ሠመራ የተካሄደውን ሕዝባዊ ውይይት የመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰውን(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የአንዱ ክልል አመራር ወደ ሌላኛው ክልል ሄዶ ሕዝቡን ፊት ለፊት አግኝቶ ማወያየት ቀደም ሲል ያልነበረ በለውጡ መንግሥት የመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደዚህ ዓይነት አካሄድ ከፋፋይ ትርክትን ለማስወገድ እና አሰባሳቢ ትርክት ለማንበር ትልቅ ዕድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ከሕብረተሰቡ ጋር ቀርቦ መወያየት መተማመንን ያዳብራል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እንደ መንግሥት የተያዙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እስከታች ወርደው እየተፈጸሙ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።
ለአብነትም በሎጊያ ሠመራ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ሰፋፊ የእርሻ ልማትና የሌማት ትሩፋት አካል የሆኑ ተግባራት በሚፈለገው ልክ እየተከናወኑ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ ተግባራትም ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ እና ለሀገር ብልጽግና መረጋገጥ መሠረት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በውይይቱ ተሳታፊዎች ዘንድ ከመንገድ፣ ከውኃ፣ ከሥራ እድል ፈጠራ፣ ከአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ጋር የተያያዙና መሰል ጥያቄዎች መነሳታቸውን አመላክተዋል።
በአጠቃላይ ሕዝባዊ ውይይቶቹ ሕዝቡ ከመንግሥት ምን እንደሚፈልግ፣ በየአካባቢው የጎደለው ነገር ምንድን እንደሆነ እና የአመራር ሥርዓታችን ምን መሆን አለበት የሚሉትን በግልጽ ያመላከቱ ናቸው ብለዋል።
እኛ ሐሳባችንን አስረድተናል፤ ሕዝቡም ሐሳቡን አስረድቶናል ከመድረኩ ለቀጣይ ተግባራት ግብዓት የሚሆኑ በቂ ሐሳቦችን ሸምተንበታል ሲሉም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት።