ቀጥታ፡

ህዝባዊ ውይይቶቹ የኢትዮጵያ ማንሰራራት በተጨባጭ ህዝብ ጋር መኖሩን ያረጋገጥንበት ነው - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የተካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች የኢትዮጵያ ማንሰራራት በተጨባጭ ህዝብ ጋር መኖሩን ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡

ከተካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች ተጨማሪ አቅም እና ጉልበት አግኝተንባቸዋል ሲሉም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

"‎የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ህዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡

በሆሳዕና ከተማ በነበረው ህዝባዊ ውይይት ላይ የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ ከህዝባዊ ውይይቶቹ የኢትዮጵያ ማንሰራራት በተጨባጭ ህዝብ ጋር መኖሩን ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ ህዝቡን በቀጥታ የማግኘትና ማወያየት ባህል ሆኖ መቀጠሉንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ የነበረው መድረክ፤ ህዝቡ ሀሳቡን እና ያለውን ጥያቄ በነጻነት ያንጸባረቀበት እንደነበር ጠቁመው ይህም ተጨማሪ አቅም እና ጉልበት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል፡፡

ኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማ ልማትና መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የመጣው ለውጥ በህዝቡ በስፋት መነሳቱንና አድናቆት የተቸረው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ ብሎም በከተማዋ የስራ አጥነት ችግር መኖሩንና ይህ እንዲፈታ መጠየቁን አስታውሰዋል፡፡

በውይይቱ የተነሱ የልማት ጥያቄዎችን በሂደት ለመመለስ መግባባት ላይ መደረሱንም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡

ውይይቱ ከዚህ ቀደም ተጠይቀው የነበሩ ጉዳዮች ምን ላይ እንደደረሱ ቀድሞ ማብራርያ የተሰጠበት መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመው ይህም መንግስት ህዝቡን እያዳመጠ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም