የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እያቃለለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እያቃለለ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያቃለለ መሆኑን የከተማው ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።
በተያዘው የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰቡን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተመላክቷል።
በመምሪያው የወጣቶች ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ደሳለኝ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ በክረምትና በበጋ ወራት የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እያቃለሉ ነው።
በተያዘው የበጋ ወራት ከ12ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ ታቅዶ እስካሁንም ከ9ሺህ 300 በላይ በጎ ፈቃደኞች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 130 ዩኒት ደም የማሰባሰብ፣ የአረጋዊያንን ቤት የማደስና በአዲስ መልክ የመገንባት እንዲሁም የአካባቢ ጽዳትና የሰብል ማሰባሰብ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ እንቅስቃሴም ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ወጪን ማዳን እንደተቻለም አቶ ደሳለኝ ጠቅሰዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፣ በአገልግሎቱ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የበርካታ ወገኖችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያቃለሉ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣት ዳዊት ይደነቅ በበኩሉ እንዳለው፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበረሰቡን ማገዙ ከፈጠረለት ውስጣዊ እርካታ በተጨማሪ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት አስችሎታል።
በዚህ ተሳትፎው ሌሎች ወገኖች ደም እንዲለግሱ ከማስተባበር ባለፈ እራሱም ደም በመለገስ በደም አቅርቦት እጥረት ለአደጋ የሚጋለጡ ወገኖችን ህይወት እየታደገ መሆኑን ተናግሯል።
በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ሥራው በአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት ላይ መሳተፉን የተናገረው ደግሞ ወጣት ምህረቱ ያዜ ነው።
በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል እማሆይ ማናህሎሽ እርታ እንዳሉት በጎ ፈቃደኞች ባደረጉላቸው የቤት እድሳት ከብርድና ከዝናብ ታድገዋቸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተከናወኑ ተግባራት ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ወጭን ማዳን እንደተቻለ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።