በሕዝባዊ ውይይቱ ለቀጣይ ሥራዎች ስንቅና ጉልበት የሚሆኑ ሐሳቦች ተስተጋብተዋል - ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በሕዝባዊ ውይይቱ ለቀጣይ ሥራዎች ስንቅና ጉልበት የሚሆኑ ሐሳቦች ተስተጋብተዋል - ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018 (ኢዜአ)፡- በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ መድረክ ለቀጣይ ሥራዎች ስንቅና ጉልበት የሚሆኑ ሐሳቦች በስፋት መነሳታቸውን የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳን(ዶ/ር) ተናገሩ።
"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ህዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡
የተካሄዱትን ሕዝባዊ ውይይቶች አንድምታ አስመልክቶ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል።
በዚህ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ የተካሄደውን ሕዝባዊ ውይይት መምራታቸውን አውስተዋል።
በውይይቱ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ በርካታ ሰዎች ማለትም ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና የመንግስት ሰራተኞች በንቃት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ተሳታፊዎች የተሠሩትን ሥራዎች ማድነቃቸውንና እንዲስተካከል የሚፈልጉትንም መጠቆማቸውን ነው የጠቀሱት።
የጉባ ብሥራቶችን ጨምሮ የባሕር በር ጉዳይ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሳኩ የሚጠይቁ ሐሳቦች በስፋት መስተጋባታቸውንም ተናግረዋል።
እነዚህ አስተያየቶች ደግሞ የበለጠ ቁጭት እና ተነሳሽነት የሚፈጥሩ በመሆናቸው፤ ለቀጣይ ሀገራዊ ሥራዎች ስንቅና ጉልበት ስለሚሆኑ በግብዓትነት ይወሰዳሉ ሲሉም ገልጸዋል።