በክልሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን በድምቀት ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን በድምቀት ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል
ባህር ዳር፤ ታህሳስ 12/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የገና እና የጥምቀት በዓላትን ጨምሮ ሌሎች ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን በድምቀት ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ እምቢያለ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ በየዓመቱ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት የቱሪስት ፍሰትንና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የጎላ ሚና አላቸው።
በተለይም በላሊበላ የገና በዓል እንዲሁም በጎንደር፣ በባህርዳር እና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበሩት የከተራና የጥምቀት በዓላት በዋናነት እንደሚጠቀሱ አንስተዋል።
በተጨማሪም በጥር ወር በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መኖራቸውንና ለማሳያነትም የአገው ፈረሰኞች በዓል በእንጅባራ፣ በጣና ሐይቅ ላይ የሚካሄደው የታንኳ ቀዘፋ ውድድርና እና ሌሎችም ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዓላቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ከአመራሮችና የሃይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በየአካባቢው በዓላቱን በድምቀት ማክበር እንዲቻልም ዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው የበዓል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በዓላቱን ለመታደም የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የሚያርፉባቸው ሆቴሎች ለእንግዶች የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ አበበ ተናግረዋል።
በላሊበላና በጎንደር በሚከበሩ በዓላት ለሚታደሙ ቱሪስቶች ተጨማሪ በረራዎች እንዲመደቡ ቢሮው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም አመልክተዋል።