ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር ትገናኝበት የነበረውን የባሕር በር ባለቤትነት መጠየቋ ህጋዊ መሰረት ያለው ነው - ምሁራን

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 12/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነቷን እንዳታስመልስ የሚደረጉ ጥረቶች ተገቢ አለመሆናቸውንና ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር ትገናኝበት የነበረውን የባሕር በር ባለቤትነት መጠየቋ ሕጋዊ መሠረት እንዳለው ምሁራን አስገነዘቡ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት የሚደረገው ጥረት የትውልድ ጥያቄ መሆኑን በመግለጽ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን እና ተመራማሪ አበበ አኖ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት ጋር ትገናኝበት የነበረውን የባሕር በር መጠየቋ መሠረታዊ ጥያቄ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በነበራት የባሕር በር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጋር በንግድ፣ በጉብኝት እንዲሁም በሌሎች ሥራዎች ጥብቅ ቁርኝት እንደነበራት አውስተው፤ ይህንም ታሪክ እንደሚመሠክር አስረድተዋል።

ነገር ግን ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በተፈጸመ ታሪካዊ ስኅተት የነበራትን የባሕር በር እንድታጣ መደረጉ አስቆጭም፤ አሳዛኝም ነው ብለዋል።

የሆነው ሆኖ የባሕር በሯ የተወሰደበትም ሆነ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም የተባለበት ሁኔታ ቢያስቆጭም፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት ታምኖ በአሁኑ ትውልድ ጥረቶች መጀመራቸው ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ያህል ታሪካዊ፣ ትልቅና የበርካታ ሕዝብ ባለቤት የሆነች ሀገር የባሕር በር እንዳይኖራት የሚያደርጉ ሂደቶች ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቅቡልነት እንደሌላቸው በአጽንኦት ያነሱት ደግሞ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-አመራርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌትዬ ትርፌ(ዶ/ር) ናቸው።

ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበው፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ያለው ጥረት በታሪካዊ ዳራ፣ ሕጋዊ ሠነዶች፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕጎች መለኪያነት ቅቡል እና አሳማኝ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ያለውን የባሕር በር ለማግኘት ኢትዮጵያ ያነሳችው ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችበት ምክንያት ሴራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር፣ የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተመራማሪና ደራሲ ዳዊት መዝገበ ናቸው።

ሀገራዊ ብሎም ቀጣናዊ ትሥሥርን ከማጠናከር አኳያ የባሕር በር ለማግኘት የሚደረግ ጥረት የትውልድ ጥያቄ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት በማመን ጥረቶች መጀመሯ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፤ ለሕዝቦች ትሥሥር፣ ከሀገር አልፎ ለቀጣናዊ ትብብርና በጋራ ለማደግ የባሕር በር ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ለቀጣናው ከሚኖረው ፋይዳ፣ የጋራ ዕድገትና ልማት አንጻር ሀገራት ቢተባበሩ እንደሚያተርፉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሕጋዊ መሠረት፣ ታሪካዊ እና የሠነድ ማስረጃ በአግባቡ ሠድራ በሰላማዊ የዲፕሎማሲ ልዕልና ስልት ጥረቷን በይበልጥ አጠናክራ መቀጠል እንደሚጠበቅባትም መክረዋል።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት ተቀምጣ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ይዛ የበይ ተመልካች ልትሆን እንደማይገባም ነው ምሁራኑ ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም