በአፍሪካ ዋንጫ ልንመለከታቸው የሚገቡ አምስት ተጫዋቾች - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዋንጫ ልንመለከታቸው የሚገቡ አምስት ተጫዋቾች
በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይጀመራል።
በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት በስድስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአፍሪካ ዋንጫው 667 ተጫዋቾች ተሳትፎ ያደርጋሉ።
በውድድሩ ላይ የብዙዎችን ትኩረት የሳቡትን አምስት ተጫዋቾች እንመለከታለን።
1/ ቪክቶር ኦሲሜን (ናይጄሪያ)
በአውሮፓ እግር ኳስ ስማቸው ገኖ ከሚሰሙ የአፍሪካ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች መካከል አንዱ ቪክቶር ኦሲሜን ነው።
የ26 ዓመቱ ተጫዋች ከእ.አ.አ 2020 እስከ 2025 በጣልያኑ ናፖሊ ድንቅ ጊዜ አሳልፏል። በ108 ጨዋታዎች 65 ግቦችን አስቆጥሯል። በአሁኑ ሰዓት ለተርኪዬ ክለብ ጋላታሳራይ በመጫወት ላይ ይገኛል።
ኦሲሜን ለናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ከእ.አ.አ 2017 አንስቶ እየተጫወተ ነው። ለንስሮቹ 45 ጨዋታዎችን 31 ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ለሀገሩ አለኝታነቱን አስመስክሯል።
ናይጄሪዊው አጥቂ ከናይጄሪያ ጋር አህጉራዊውን ክብሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ይጫወታል። ሀገሩም የሱን ግቦችን ማስቆጠር ትጠብቃለች።
2/ አሽራፍ ሃኪሚ (ሞሮኮ)
ሌላኛው በአፍሪካ ዋንጫ የምንመለከተው ተጫዋች የአዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ ተጫዋች አሽራፍ ሃኪሚ ነው።
በዓለማችን ከሚገኙ የቀኝ መስመር ተመላላሽ ተጫዋቾች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ሃኪሚ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ድንቅ ጊዜን አሳልፏል። የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ አራት ዋንጫዎችን አንስቷል። የ26 ዓመቱ ተጫዋች ግብ በማስቆጠር እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በዚህ ድንቅ ብቃቱ የ2025 የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አግኝቷል። ተጫዋቹ በአሁኑ ሰዓት በጉዳት ላይ ቢገኝም እያገገመበት ያለው ፍጥነት መሻሻል የታየበት መሆኑ በብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች ላይ የመሳተፍ እድሉ ጨምሯል።
የሞሮኮ አምበል ሃኪሚ ለሀገሩ 88 ጨዋታዎችን አድርጎ 11 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። ሃኪሚ ከሞሮኮ ጋር የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳትን ያልማል።
3/ ሳዲዮ ማኔ (ሴኔጋል)
. አፍሪካ ከምትኮራባቸው ኮከቦቿ መካከል አንዱ የ33 ዓመቱ የክንፍ መስመር ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ ነው።
ሳዲዮ ማኔ በአውሮፓ ክለቦች በነበረው ቆይታ ድንቅ ጊዜን አሳልፏል። በተለይም ከእ.አ.አ 2016 እስከ 2022 በሊቨርፑል የነበረው ቆይታ የሚዘነጋ አይደለም። ቡድኑ ማልያ ባደረጋቸው 196 ጨዋታዎች 90 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ማኔ የአውሮፓ ቆይታውን እ.አ.አ 2023 አጠናቆ ወደ ሳዑዲ አረቢያው አል ናስር በማምራት እየተጫወተ ይገኛል።
በካሜሮን አስተናጋጅነት እ.አ.አ 2021 በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋል ግብጽን በፍጻሜው አሸንፋ የመጀመሪያ ዋንጫዋን ስታነሳ የቡድኑ አባል ነበር። ለሀገሩ እስከ አሁን ባደረጋቸው 119 ጨዋታዎች 51 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። ማኔ ከሀገሩ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካን ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማል።
4/ ብሪያን ምቡዌሞ (ካሜሮን)
የግራ እግሩ ባለ ክህሎት ተጫዋች ብሪያን ምቡዌሞ በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ይደምቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።
ምቡዌሞ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በ71 ሚሊዮን ፓውንድ ከብሬንትፎርድ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ በአምስት ዓመት ውል ካመራ በኋላ ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። በሊጉ ስድስት ግቦችን አስቆጥሯል።
የ26 ዓመቱ ካሜሮናዊ ከእ.አ.አ 2022 አንስቶ ለሀገሩ እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን 27 ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባት ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ምቡዌሞ እ.አ.አ በ2021 በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ያደረገ ሲሆን ቡድኑ በወቅቱ እስከ ጥሎ ማለፍ ጉዞ አድርጓል። በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በቁርጭምጭሚት ጉዳት ምክንያት አልተጫወተም። በሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ከካሜሮን ጋር የተሻለ ጎዞ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
5/ መሐመድ ሳላህ (ግብጽ)
የ33 ዓመቱ መሐመድ ሳላህ የአፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮከብ ነው። ተጫዋቹ ለግብጽ ብሄራዊ ቡድን እና ሊቨርፑል ቁልፍ የሚባል ተጫዋች መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።
ከእ.አ.አ 2011 አንስቶ ለግብጽ እየተጫወተ የሚገኘው ሳላህ ለሀገሩ ባደረጋቸው 109 ጨዋታዎች 63 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ለሊቨርፑል እስከ አሁን ባደረጋቸው 302 ጨዋታዎች 188 ግቦችን በማስቆጠር የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል።
ተጫዋቹ ከሀገሩ ጋር የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ለማንሳት ይጫወታል። ግቦችን ማስቆጠር፣ የግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል፣ የሜዳ ላይ መሪነት እና በትልቅ ጨዋታዎች ላይ ያለው ወሳኝነት የተጫዋቹ መገለጫ ናቸው።
የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ፣ የናይጄሪያው አዴሞላ ሉክማን፣ የዛምቢያው ፓትሰን ዳካ፣ የዩጋንዳው አለን ኦኬሎ እና የማሊው ማህመዱ ዶኩሬ ሌሎች በአፍሪካ ዋንጫው የሚጠበቁ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው።