ቀጥታ፡

አንዳንድ እውነታዎች ስለ 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ !

35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነገ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይጀመራል።የአፍሪካ ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር ለ29 ቀናት ይካሄዳል።

የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ፦

✍️ሞሮኮ 35ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታስተናግድ የተመረጠችው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በዝግጅት ማነስ ምክንያት የጊኒን የአዘጋጅነት መብት መውሰዱን ተከትሎ ነው። ሞሮኮ እ.አ.አ 1988 ካዘጋጀችው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ውድድሩን ስታዘጋጅ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

✍️የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ከሌሎቹ ውድድሮች የሚለየው በፈረንጆች ገና እና አዲስ ዓመት ወቅት መደረጉ ነው። ይህም የሆነው በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

✍️በአፍሪካ ዋንጫው ላይ 24 ሀገራት በድስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ከ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ 24 ሀገራት በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ ይገኛል። ከ670 በላይ ተጫዋቾችን ጨምሮ ከእንድ ሺህ በላይ የቡድን አባላት በውድድሩ ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

✍️በሞሮኮ ስድስት ከተሞች በሚገኙ ዘጠኝ ስታዲየሞች 52 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ራባት፣ ካዛብላንካ፣ ማራካሽ፣ ታንጂየር፣ አጋዲር እና ፌዝ ጨዋታዎቹ የሚደረጉባቸው ከተሞች ነው። ስታዲየሞቹ በአጠቃላይ ከ386 ሺህ በላይ ተመልካቾች የማስተናገድ አቅም አላቸው።

✍️ሙሉ እድሳት የተደረገለት ፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም የመክፈቻ እና የፍጻሜ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። በራባት የሚገኘው እና 69 ሺህ 500 ተመልካች የሚይዘው ስታዲየም ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማት በሚል እየተሞከሸ ይገኛል። ይህም የሞሮኮን ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማቶች የሚያሳይ ነው። ሞሮኮ ለስታዲየሞች እድሳት እና ግንባታ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች።

✍️ለ52 ጨዋታዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ትኬቶች መሸጣቸው በውድድሩ ታሪክ ክብረ ወሰን መሆኑን ካፍ አስታውቋል። ይህም የእግር ኳስ አፍሪካያን ለውድድሩ የሰጡትን ከፍተኛ ትኩረት ያሳያል። በተጨማሪም ውድድሩ ከ150 በላይ ሀገራት የሚገኙ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በቴሌቪዥን መስኮታቸው ይመለከቱታል ተብሎ ይጠበቃል።

✍️ካፍ በአጠቃላይ ለውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት የ32 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን ዋንጫውን የሚያነሳው ቡድን የሰባት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል። የገንዘብ ሽልማቱ ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት እና እድገት የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

✍️የአፍሪካ ዋንጫው ምልክት (ማስኮት) “አሳድ” የሚል ስያሜ አለው። አሳድ በአትላንት አንበሶች የተመሰለ ሲሆን የጥንካሬ፣ ኩራት እና የአፍሪካ ማንነት ምልክት እንደሆነ ተገልጿል።

✍️ለውድድሩ የተዘጋጀችውን ኳስ ያቀረበው ፑማ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ነው። ይህም በካፍ እና በፑማ መካከል ያለውን አጋርነት እየተጠናከረ መምጣት ያሳያል።

✍️ሞሮኮ በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ነው የተባበለትን የ“4K HDR” የቀጥታ የጨዋታ ስርጭት ሙከራ ታደርጋለች። “4K HDR” በዓለም አቀፍ የብሮድካስት ኩባንያዎች ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን የምስል ጥራቱ ከፍተኛ የሆነ ነው።

✍️ቀረጻው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርጹ ካሜራዎች እና ድሮኖችን ያካተተ ነው።ዓለም አቀፍ “4K HDR” የብሮድካስት ስርጭት ስርዓቱ ከዓለም ዋንጫ ጋር ተቀራራቢነት ያለው እንደሆነ ተነግሯል።

✍️የአፍሪካ ዋንጫው በሞሮኮ የቱሪዝም ወቅት ውስጥ ከፍተኛ ጎብኚ በሚመጣበት ጊዜ መካሄዱ ለቱሪዝም እድገት እና ለሀገር ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

✍️ሞሮኮ በ2025 የመጀመሪያ 10 ወራት ከቱሪዝም ከ11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘች ሲሆን የአፍሪካ ዋንጫ ይሄን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።

✍️የአፍሪካ ዋንጫን ለመዘገብ 3 ሺህ 800 ያህል ገደማ መገናኛ ፈቃድ ማግኘታቸውን ካፍ አስታውቋል።

✍️35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም