ቀጥታ፡

ስታርት አፕና የዲጂታል ክህሎት ልማት ለዲጂታል 2030 ስትራቴጂ መሳካት ትልቅ ሚና ከሚጫወቱ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ ስታርት አፕና የዲጂታል ክህሎት ልማት ለዲጂታል 2030 ስትራቴጂ መሳካት ትልቅ ሚና ከሚጫወቱ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ሙሉቀን ቀሬ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ሙሉቀን ቀሬ በተለይ የዲጂታል ክህሎትን ለማሳደግ ወሳኝ አቀጣጫዎች ተቀምጠዋል ብለዋል።

በዚህም በ2030 ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 70 በመቶ የሚሆነው የዲጂታል እውቀት እንዲኖረው፣ 80 በመቶ የሚሆነው የመንግስት ሰራተኛ የዲጂታል ክህሎት የተላበሰ እንዲሆን፣ 10 ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል ስልጠና እንዲወስዱ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ይሆናል ነው ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪ 5 ሺህ ስታርት አፖች ወደ ስራ እንዲገቡና በዲጂታል ዘርፍ ለ1 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠርም እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በ2030 ከሀገር ወስጥ አጠቃላይ ምርት ዲጂታል ዘርፍ ገቢ 12 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጨመረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም