ቀጥታ፡

ዲጂታላይዜሽን የብልጽግና ግብ ማሳኪያ ቁልፍ መሳሪያ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የዲጂታል ዘርፉን ተደራሽነት በማስፋት የብልጽግና ግብ ማሳኪያ ቁልፍ መሳሪያ አድርጎ እየሰራበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሊቀ መንበር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሊቀ መንበር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የማደግ ፍላጎትና አቅም ያላት ሀገር ናት።

የኢትዮጵያ ዲጂታል መርሃ ግብርም በፈጠራና ፍጥነት እመርታን በማምጣት የማደግ ፍላጎትን ከአቅም ጋር እንዲናበብ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የለውጡ መንግስት የዲጂታል ዘርፍ እንደአስቻይ አቅም ብቻ የሚታይበትን የቀደመ እይታ ከፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ዘርፉን ለሁሉም መስክ ተደራሽ በማድረግ አንደኛው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽና የብልጽግና መዳረሻ ግብን በእጅጉ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

ከአምስት ዓመታት በፊት መተግበር የተጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂም የዲጂታል መሠረቶችን በማስቀመጥ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎችን ለማከናወን ገንቢ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በማስፋት ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ማስገኘቱንም ነው የተናገሩት።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ በመንግስት አሰራር፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በቴሌኮም ዘርፍ፣ በኃይል አቅርቦትና በፋይናንስ ተደራሽነት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገሩን ገልጸዋል።


 

በተለይም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውጥኖችን የሚያግዙ የፋይናንስ፣ የሰው ሀብት ልማትና ፖሊሲ ትግበራ አቅምን ማሳደግ የሚሹ ሦስት ጉዳዮች ላይ አመርቂ ውጤት ማምጣቱን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያን ወደ ዲጂታል 2030 ማሸጋገር ያስቻለ አመርቂ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አንስተዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሁሉን አቀፍና አካታች የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብና የውስጥ ፈጠራን በማበረታታት ሙሉ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት ከተለመዱ ተፈጥሯዊ አካሄዶች ባለፈ የመፍጠን፣ መዝለልና የፈጠራ ማዕከሎችን በመያዝ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ታሳቢነት የተቀረጸው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም የመንግስትን ልዩ ትኩረት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላትና የማኅበረሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም