ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽ፣ ፍትሃዊ እና አስተማማኝ የዲጂታል ምህዳር መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽ፣ ፍትሃዊ እና አስተማማኝ የዲጂታል ምህዳር መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽ፣ ፍትሃዊ እና አስተማማኝ የዲጂታል ምህዳር መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተሳክቷል።
በተለይም በህዝብ መገልገያ ዲጂታል መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ ውጤታማ ስራ መከናወኑን አንስተዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ ወሳኝ በሚባል ደረጃ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት መሸጋገሯን ጠቅሰው፤ በዚህም ገንዘብ ለማሳተም የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት መቻሉን አብራርተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ም ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን መሰረት በማድረግ መዘጋጀቱን አንስተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሦስት ቁልፍ ትልሞች እንዳሉት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህም ተደራሽነትን ማስፋት፤ እኩል እድል ማመቻቸትና በተቋማትና ህዝብ መካከል መተማመንን መፍጠር መሆናቸውን አብራርተዋል።
እነዚህን ትልሞች ለማሳካት ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም ትስስር ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ይህም እድገትን ከማሳለጥ ባሻገር በየአካባቢው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ስትራቴጂው ለህዝብ መገልገያ ዲጂታል መሰረተ ልማት መስፋፋት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሚከናወኑ ሥራዎች በጠንካራ የሳይበር ደህንነት ሊታገዙ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ አበረታች ሥራ መከናወኑን አንስተው፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ተቋም ተገንብቷል ብለዋል።
የሳይበር ደህንነት ሥራውም የዲጂታል ስርዓት፣ የዲጂታል መረጃንና ትውልዱን መጠበቅ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።
በተለይ የትውልዱ የዲጂታል አጠቃቀም ከኢትዮጵያ ባህል፣ እሴትና ሉዓላዊነት ጋር በተናበበ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እንዲሳካም ሁሉም በትብብር መስራት እንዳለበት ነው ጥሪ ያቀረቡት።