ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሚናችንን እናጠናክራለን - የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሚናችንን እናጠናክራለን - የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች
ወልዲያ፤ ታሕሳስ 11/2018(ኢዜአ)፡ - በዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ በንቃት በመሳተፍ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሰሜን ወሎ ዞንና የወልዲያ ከተማ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
''ዘካሪ፣ መካሪ የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላምና ልማት'' በሚል መሪ ሃሳብ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በወልዲያ ከተማ ተካሄዷል።
ከመድረኩ ተሳተፊዎች መካከል አቶ ጎበዜ እሸቱ፤ ችግሮች ለመፍታት በጋራ በመመካከርና መፍትሄ በማበጀት ተመራጭና ተገቢ ነው ብለዋል።
በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል እኛ የሃገር ሽማግሌዎች የጎላ ሚናችንን በመወጣት እያበረከትነው ያለውን ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል።
የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ለሰላም ግንባታው ምቹ ሁኔታ እንደሆነ አንስተው፤ በጫካ የቀሩትም እንዲመለሱ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
አቶ ደምሌ ሲሳይ በበኩላቸው፤ እርስ በርስ መጎዳዳት የክልሉን ሕዝብ የማይመጥን ተግባር በመሆኑ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ እገዛችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የሰላም ግንባታ ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው እንዳልሆነ የጠቀሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች ፤ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ በንቃት በመሳተፍ ሕብረተሰቡን አስተባብረው ሚናቸውን አጠናከረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ንጉስ ዝናቡ ፤ በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ የሕግ የበላይነትን በማስከበር በከተማው ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም መስፈን እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ በክልሉ በሕግ ማስከበር እርምጃ የሰፈነው ሰላም ለማፅናት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የወልዲያንና አካባቢውን ሰላም ለማስከበር የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በመድረኩ የወልዲያ ከተማና የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።