ቀጥታ፡

ሰራተኛው በአካልብቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ ተነቃቅቶ ውጤታማነቱን ለማጠናከር የሚያግዝ ዓመታዊ የጤና ስፖርት ውድድር ተጀመረ

ባሕርዳር፤ ታሕሳስ 11/2018(ኢዜአ)፡-  ሰራተኛው  በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ ተነቃቅቶ በየተሰማራበት መስክ ውጤታማነቱን  ለማጠናከር  የሚያግዝ  ዓመታዊ የጤና ስፖርት ውድድር ዛሬ  በባሕርዳር ከተማ ተጀመረ። 

ከ40 በላይ የግልና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች የሚሳተፉበት  የጤና ስፖርት ውድድሩ የሚካሄደው "ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት" በሚል መሪ ሃሳብ  ነው።


 

ከተቋማቱ የተውጣጡ ከአንድ ሽህ 200 በላይ ሰራተኞች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

የባሕርዳር  ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቶማስ ታምሩ በውድድሩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤  የውድድሩ  ዓላማ ሰራተኛው በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ ተነቃቅቶ የተቀላጠፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማገዝ ነው። 

የተቋማት የእርስ በርስ ግንኙነትን አጠናክሮ ቅንጅታዊ አሰራርን በማዳበርና ሰራተኛው በተሰማራበት ስራ ሁሉ የላቀ አፈጻጸም እንዲያስመዘግብም እንዲሁ። 

ውድድሩ የተጀመረው የከተማ አስተዳደሩና የክልል የዘርፉ አመራሮች በተገኙበት በባሕዳር ዩኒቨርሲቲና በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን(አሚኮ)  መካከል በእግር ኳስ ጨዋታ ነው። 

እስከ ስድስት ወራት  የሚዘልቀው የጤና ስፖርት ወድድሩ  ከእግር ኳስ በተጨማሪ ቦሊቦል፣ ጠረጴዛ  ቴንስ፣ ዳርትና ቼዝ እንደሚያካትት ተመላክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም