ቀጥታ፡

ማንችስተር ሲቲ ዌስትሃም ዩናይትድን በማሸነፍ የሊጉ መሪ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ማንችስተር ሲቲ ዌስትሃም ዩናይትድን 3 ለ 0 አሸንፏል። 

ማምሻውን በኢትሃድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አርሊንግ ሃላንድ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ቲጃኒ ራይንደርስ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

በሊጉ 12ኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ሲቲ ነጥቡን ወደ 37 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት በጊዜያዊነት ከአርሰናል ተረክቧል። 

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ዌስትሃም ዩናይትድ በ13 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ሃላንድ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 19 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቱን አጠናክሯል።

በሌሎች ጨዋታዎች ብሬንትፎርድ ዎልቭስን 2 ለ 0 አሸንፏል። በርንሌይ ከቦርንማውዝ አንድ አቻ ሲለያዩ ብራይተን ከሰንደርላንድ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። 

አርሰናል ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ከሜዳው ውጪ ከኤቨርተን ጋር ይጫወታል። ካሸነፈ በድጋሚ የሊጉ መሪ ይሆናል።

ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ30 ላይ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከሊቨርፑል እና ሊድስ ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ ምሽት አምስት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም