ቀጥታ፡

የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረውን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የትግበራ ምዕራፍ ዛሬ በይፋ አስጀምረናል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምርጫ ሳይሆን ግዴታችን ነው።

ላለፉት አምስት ዓመታት ስንተገብረው የቆየነው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሀገራችንን በቴክኖሎጂ የታገዘ የኢኮኖሚ መሠረት ላይ ለማቆም ያስቻሉ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

ከተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች መካከልም የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የሳይበር ምህዳር ደህንነት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ ዲጂታል ፋይናንስና ክፍያ፣ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ዲጂታል ክህሎት የተላበሰ ብቁ ዜጋ መፍጠር ተጠቃሽ ናቸው።


 

አዲሱ ስትራቴጂ በተቀናጀ አመራርና በጠንካራ መዋቅር የሚመራ ሀገራዊ ስትራቴጂ ነው። ስትራተጂው ሁሉን አቀፍና አካታች የዲጂታል አገልግሎቶችን ተደራሽ ያደርጋል፤ ዜጎችን ማዕከል ያደረገ ዲጂታል መንግሥት ይገነባል፤ የሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችንና ስታርታፖችን ያበረታታል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት ከተለመደው አካሄድ ወጥተን፣ በፈጠራና በፍጥነት የታጀበ የዲጂታል ዝላይ ጉዞ ማድረግን ይጠይቃል።

ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ተቋማትና የግሉ ዘርፍ አገልግሎታቸውን ይበልጥ በማዘመን፣ የልማት አጋሮች ድጋፋቸውን ከስትራቴጂያችን ጋር በማጣጣም፣ ወጣቶችና ባለሙያዎች በፈጠራ አቅማቸው ሀገራዊ መፍትሔዎችን በማመንጨት፣ የድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ እላለሁ።

የኢትዮጵያን ብልፅግና በዲጂታል እውቀትና ፈጠራ እናሳካዋለን።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም