ቀጥታ፡

በምእራብ ወለጋ ዞን ሠላምን በማስፈን ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን እንደግፋለን --ነዋሪዎች

ጊምቢ፤ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፡-በምእራብ ወለጋ ዞን ሠላምን በማስፈን  ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን እንደግፋለን ሲሉ በጊምቢ ከተማ በተካሄደ ህዝባዊ ውይይት ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ገለጹ።

''የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች'' በሚል መሪ ሃሳብ በዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ህዝባዊ ውይይት በጊምቢ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎች በዞኑ ሠላምን በማስፈን ረገድ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የህዝቡን ጥያቄ የመለሱ ናቸው ብለዋል።

ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በዞኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተዋል።

በተለይም በህዝቡ ዘንድ የመልካም አስተዳዳር ችግር ሆነው የቆዩ መሰረተ ልማቶች ተቋማት ግንባታም በፍጥነት እየተከናወነ በመሆኑ መንግስትን አመስግነዋል።

በቀጣይም ሠላምን በማስፈን ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን እንደግፋለን ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም አልፎ አልፎ  የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች እልባት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመው የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ እንዲፋጠን ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ህገ -ወጥ ንግድን ጨምሮ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ተግባራትን የመቆጣጠር ስራ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ፣ የለወጡ መንግስት የህዝቡን ሁሉንተናዊ ህይወት ለማሻሻል እየተጋ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ህዝቡ ትኩረቱን ልማት ላይ እንዲያደርግ ማስቻሉን ገልጸው የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታም በስፋት መከናወኑን አንስተዋል።

መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የሚጠናከሩ ሲሆን የኑሮ ውድነትን ለመቀነስም ሰፋፊ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ ብለዋል።


 

የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፋ በበኩላቸው በዞኑ ሰላምን በማፅናት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ቀጥለዋል ብለዋል።

በዞኑ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን ማጠናከር እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቀነስ ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም