ቀጥታ፡

ፍልሰት በአግባቡ ካልተመራ በዜጎችና ሀገር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል

ወላይታ ሶዶ፤ታሕሳስ 11/2018 (ኢዜአ)፡- ፍልሰት በአግባቡ ካልተመራ በዜጎችና ሀገር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ተገልጿል።

በመሆኑም ፍልሰትን ወጥ በሆነ መንገድ በአግባቡ ለማስተዳደር የሁሉም ባለደርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ተብሏል።

"የዜጎች ፍልሰትን ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ኮንፈረንስ ዛሬ በሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በኮንፍረንሱ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፈሰር ክንደያ ገብረህይወት በመድረኩ እንዳሉት፤ ፍልሰት በአግባቡ ካልተመራ በዜጎችና ሀገር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል።

ሆኖም በአግባቡ ማስተዳደር ከተቻለ የዜጎችንና የሀገርን ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

ፍልሰትን በአግባቡ ለማስተዳደር የሁሉም ባለደርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምር በማድረግ ፍልሰትን ወጥ በሆነ መንገድ ማስተዳደር ለሚያስችል ፖሊሲ ግብአት ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።

ፍልሰትን በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል በምርምር የታገዘ ስርዓት እንዲበጅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚናን ለማጎልበት ሚኒስቴሩ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዘውድነህ ቶማስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ፍልሰትን በምርምርና ጥናት በማገዝ ለዘላቂ ልማት ለማዋል ከአርባምንጭ፣ ዲላ እና ጂንካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብረው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ የግብርና፣ የማዕድን፣ ኢንዱስትሪና የቱሪዝም ልማት አካታችና ትርጉም ባለው መንገድ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ካሠች ኤልያስ፤ ፍልሰትን ለዘላቂ ልማት ለማዋል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጀመረው ጥረት የዘርፉን ችግር ለማቃለል አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ ፍልሰትን ለማስቆም ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ በፍልሰት ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም