በኢሉአባቦር ዞን ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ድሎች እንዲቀጥሉ የድርሻችንን እንወጣለን --ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኢሉአባቦር ዞን ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ድሎች እንዲቀጥሉ የድርሻችንን እንወጣለን --ነዋሪዎች
መቱ ፤ታህሳስ 11/2018 (ኢዜአ)፡- በኢሉአባቦር ዞን ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ድሎች እንዲቀጥሉ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በመቱ ከተማ በተካሄደ ህዝባዊ ውይይት ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ገለጹ።
''የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ ከመቱ ከተማና ከኢሉአባቦር ዞን ወረዳዎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን ያሳተፈ ህዝባዊ ውይይት በመቱ ከተማ ተካሄዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የዞኑን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ ታላላቅ የልማት ውጤቶች መመዝገብ ችለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የመቱ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሼህ ኤልያስ ሙሐመድ፣ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ልማቶች በሁሉም መስክ እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
ዘመናዊ የአሰራር ዘዴን በመከተል የግብርና ልማት በመተግበሩ ትልቅ ውጤት እየተመዘገበ የሕዝብን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ታከለ ዳዲ በበኩላቸው መንግስት አንድነትን በማጽናት ልማትን ለማስፋፋት የሚያከናውነው ስራ የሚደገፍ ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ድሎች እንዲቀጥሉ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ደበላ ዶርፎ በበኩላቸው በለውጡ ዓመታት መንግስት በሰላም፣ በልማት፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎች መስኮች ያሳየው ቁርጠኝነትና የተመዘገቡ ውጤቶች የሚያስመሰግኑ ናቸው ብለዋል።
ሆኖም የዞኑንና የከተማውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉና ትኩረት የሚያሻቸው አንዳንድ ጉዳዮች አንዳሉም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
ከነዚህም መካከል የኖሌ- አልጌ- መቱ እንዲሁም የበቾ-ሳይለም-አጋሮ አስፋልት መንገዶች ግንባታ መጓተት፣ የአባቦር ስታዲየምና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ልማትን መፋጠን እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሕዝቡ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን ትልቅ ተግዳሮት በመሆኑ መፍትሔ የሚሻ መሆኑንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በዞኑ እየተተገበሩ የሚገኙ የሻይ እና የሩዝ ልማት ስራዎችን ተከትሎ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉም አንስተዋል።
በዞኑ የሚገኘው ትልቅ የሀገር ሀብትና የቱሪዝም አቅም መሆን የሚችለው የሶር ፏፏቴ ስፍራ ልማት ትኩረት እንዲደረግበትም አክለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻፊ ሁሴን፣ መንግስት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕብረተሰቡም የስራ ባሕሉን ይበልጥ በማሻሻል ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እንዲተጋ ያሳሰቡት አቶ ሻፊ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንም መትጋት ይገባል ነው ያሉት።
የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ፣ የሻይ ልማትን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮችን ለማስፋፋት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።