ቀጥታ፡

የህዳሴው ግድብ የኃይል አቅርቦት ለጤናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ትልቅ አበርክቶ አለው

አሶሳ፤ ታህሳስ 11/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ለጤናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ትልቅ አበርክቶ እንዳለው የዘርፉ አመራሮች ተናገሩ።

የጤና ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ የሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር የጤና ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች እና የሆስፒታል ስራ አስኪያጆች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገርናቸው የሥራ ኃላፊዎች እንደተናገሩት፤ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ቁጭት የመለሰ እና የይቻላል መንፈስን ያስመሰከረ ትልቅ ፕሮጀክት ነው።

ከጎብኚዎቹ መካከል የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ብርሃኑ ሰንደቅ ግድቡን ለመጀመሪያ ጊዜ እየጎበኙ መሆኑን ገልፀው፥ ለግድቡ ባደረጉት ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ግድቡ በኃይል አቅርቦት ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ትልልቅ የጤና ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የኃይል መቆራረጥ በማስቀረት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

በሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ የመድኃኒት እና ህክምና አስተዳደር ኃላፊ ነስረዲን አብዲ በበኩላቸው፤ ግድቡ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሚያስችሉ ፕሮጀከቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ህዳሴ ግድቡ ሲመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በጉባ ብስራቶች ላይ ይፋ ያደረጓቸው ፕሮጀክቶች በሶማሌ ክልል መጀመራቸውን ተናግረው፤ ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ የመልማት አቅም እንዳላት ማሳያ እንደሆኑም አብራርተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ያሉት ደግሞ  የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ጃፈር መርቀኒ እና  በሲዳማ ክልል የዳዬ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ተሻለ ታምራት ናቸው።

ግድቡ የጤና ተቋማት በቂ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ እና የጤናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል የሚያደርግ ሀገራዊ ፕሮጀክት እንደሆነ አስታውቀዋል።

አሁን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ በህዳሴው ግድብ ላይ ያሳየነውን አንድነት እና ትብብር አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም