ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ ለሌሎች ከተሞችም አርአያ የሆነና ተነሳሽነትን የፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለሌሎች ከተሞችም አርአያ የሆነና ተነሳሽነትን የፈጠረ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት አስተዳደር ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ የከተሞች የኮሪደር ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ እያካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የከተሞች ከንቲባዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።


 

የአዲስ አበባ ከተማ የኮርደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ከድር አደም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር ከ5 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል።

በዚህም ከ179 ሺህ በላይ ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩን፣ የ185 ኪሜ የአስፋልት መንገድ ግንባታ እንዲሁም 47 ኪሜ የወንዞች ልማት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ስኬት ለሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከተሞች ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ለኢንቨስትመንት ሳቢ መሆን እንዳለባቸው ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።

በወንዝ ዳርቻ ልማቶችም የከተማዋን የተፈጥሮ ኃብቶች ወደ ውብ መዝናኛዎችና አረንጓዴ ሥፍራዎች መቀየሩን ጠቁመው፤ ሥነ-ምህዳር ከመጠበቅ አኳያም የተገኙ ውጤቶች ለነዋሪዎች ጤናና ሌሎች ጠቀሜታዎችን እንዲገኙ ማድረጉን አብራርተዋል።


 

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አንዷአለም ጤናው በበኩላቸው፤የትብብር መድረኩ ከ137 በላይ ከተሞችን በአባልነት የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

የትብብር መድረኩ ከተሜነትን በማስፋፋት የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ለማበርከት በመስራት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በከተሞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችሉ አማራጮችን በመቅረጽ፣ትስስርን ማጠናከርና የከተሞች የልምድ ልውውጥ ላይ እየሰራን ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማት የከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻሉን አንስተዋል።

በንግድ፣በመኖሪያ ቤት እና በኢንዱስትሪ ዞኖች መካከል ያለውን ትስስር፣ኢንቨስትመንቶችንና ንግዶችን በመሳብ የኢኮኖሚ እድገት ከማሳደግ አንጻር ያለውን ጠቀሜታዎችም ለአብነት አንስተዋል።

ጉባኤው በኮሪደር ልማት በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ የከተሞች ተሞክሮ የመማሪያ መድረክ መፍጠርን ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ሙራድ ከድር እና የከሚሴ ከተማ ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም በሰጡት አስተያየት ከአዲስ አበባና ከሌሎች ከተሞች በኮሪደር ልማት ስራዎች ከተመለከቱት ተሞክሮዎች መሰረት በማድረግ በከተሞቻቸው ህዝቡንና የግል ባለሀብቱን በማስተባበር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም