ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ ፋሲል ከነማ ነጌሌ አርሲን በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማ ነጌሌ አርሲን 1 ለ 0 አሸንፏል። 

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ያሬድ ብርሃኑ በ66ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል። 

ምኞት ደበበ ከፋሲል ከነማ እና ካሜሮናዊው የነጌሌ አርሲ ተጫዋች ፓስካል ዴቡሲ በሁለተኛው አጋማሽ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። 

በሊጉ አምስተኛ ድሉን ያስመዘገበው ፋሲል ከነማ በ20 ነጥብ ተመሳሳይ ነጥብ ባለው የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ፋሲል ከነማ በሊጉ እስከ አሁን ሽንፈት ያላስተናገደ ብቸኛው ክለብ ነው። 

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ነጌሌ አርሲ በ13 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በአሁኑ ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም