በክልሉ ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - ወጣቶች
ደብረብርሃን፤ ታሕሳስ 11/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ወስጥ ተሳትፏቸውን በማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደብረብርሃን ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
"ለዘላቂ ሰላምና ልማት የወጣቶች ሚና " በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ከከተማው ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጥ ወጣት ዓሊ ሀሰን፣ ወጣት አንዱ ዓለም ጌታቸው እና ወጣት ወንድዬ ዘገየ በሰጡት አስተያየት፤በከተማው የተጀመሩ የልማት ስራዎች የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በመሆኑ ይህንን በማስቀጠል ሰላም በዘላቂነት ለማስከበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የሀሰት ወሬን በማጋለጥ በሰላም ግንባታ ላይ አተኩረው በመስራት ልማትን ለማፋጠን ተሳትፏቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚናቸውን እንደሚወጡም አንስተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የማሕበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማስቀጠል እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው።
ወጣቶች ሀገር ተረካቢና ትውልድ አስቀጣይ እንደመሆናቸው ይህንን በመጠበቅ ሰላምን በማፅናት ልማትን ለማፋጠን ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል ⵆ
ከባሕላዊ እሴቶች ካፈነገጡ የማህበራዊ ሚዲያ ፣ ከባዳና ባንዳዎች እኩይ እሳቤ እራሳቸውን በማራቅ ለሀገር ሰላምና ብለፅግና የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸዋም አንስተዋል።
በየዘርፉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ መንግስት አበክሮ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉ ሴቶች ፣ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ዘላለም አረጋ፤ ወጣቶች የጀመሯቸው የልማት ስራዎችን በማጠናከር የአካባቢን ፀጋ ለመጠቀም የሚያስችል እይታን ማስፋት አለባቸው ብለዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ የወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በወጣቶች ለተነሱት ጥያቄዎችና ጥቆማዎች በቀጣይ እየታየ ምላሽ በመስጠት እንደሚስተካከሉ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ከደብረ ብርሃን ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል።