ቀጥታ፡

የክልሉን ሰላም ለማናጋትና ልማትን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን እኩይ አላማ በማክሸፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-ርእሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ሰላምን ለማናጋትና ልማትን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን እኩይ አላማ በማክሸፍ በሁሉም ዘርፎች የጀመርናቸው የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።

በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሯ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፥ የጥፋት ተልእኮ ያነገቡ አካላት የክልሉን ሰላም በማናጋት መረጋጋት እንዳይኖር እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ በሰላም ወዳዱ ህዝብና በፀጥታ ሃይሉ ጠንካራ ክትትል ህግ የማስከበር ስራ እየተሰራና አጥፊዎችም በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በህግ ማስከበሩ የሀገር መከላከያና ሌሎች የፀጥታ አካላት ላደረጉትና እያደረጉ ላለው የተቀናጀ ስራ አድንቀዋል።

የክልሉን ሰላም ለማናጋትና ልማትን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን እኩይ አላማ በማክሸፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በክልሉ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥና የልማት ስራዎችን በማስቀጠል ረገድ የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠው፥ የህዝቡም እገዛና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ርእሰ መስተዳድሯ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የሁሉም የላቀ ተሳትፎና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

አጠቃላይ ህብረተሰቡ በተለይም የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ጥፋትን ማውገዝና ስለ ሰላም ማስተማር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሙላቱ ጀልዱ፤ ሰራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የሀገርን ሰላም የማስጠበቅና ህግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

ለጥፋት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ለልማት ስራዎች መሳካት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም